ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሞጣ ከተማ የተፈፀመውን ተግባር አወገዘ

ኢዜአ፤ ታህሳስ 12/2012 በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ የተፈፀመውን መስጊዶችንና ንብረት የማቃጠል ተግባር የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አወገዘ።

ምክር ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አገሪቱ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በሆነችበትና የብልጽግና ማሳያ የሆነችው ሳተላይት በመጠቀችበት ወቅት እንዲሀ አይነት ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭና የአገር ሰላም የሚያደፈርስ ተግባር መፈጸሙ ህዝበ ሙስሊሙን ያሳዘነ መሆኑን ገልጿል።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼክ ሱልጣን አማን ኤባ፤ የተፈፀመው መስጊዶችንና የሙስሊም ማህበረሰብ ንብረት የማቃጠል፣ የማውደምና የመዝረፍ ህገ ወጥ ተግባር ሊወገዝ ይገባል ብለዋል።

ድርጊቱ በሀይማኖቶች መካከል የሰፋ ልዩነትና በአገር ደረጃ ግጭት ለመፍጠር ያለመ በመሆኑ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጽኑ ያወግዘዋል ብለዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ሼህ ሃሚድ ሙሳ በበኩላቸው በሞጣ ከተማ በአንድ ቀን ውስጥ አራት መስጊዶችና የሙስሊም ንብረት  ሲወድም በዝምታ የተመለከቱ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንዲጠየቁና ከሀላፊነት እንዲነሱ አመልክተዋል።

ጥቃት የደረሰባቸው መስጊዶች ተመልሰው እንዲገነቡና ለወደመው ንብረትም ካሳ እንዲከፈል የጠየቁ ሲሆን የፌዴራል መንግስት የተፈፀሙ ጥቃቶችን በመለየት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

በአገሪቱ ያሉ ሁሉም ቤተ እምነቶች ይህን አስነዋሪ ተግባር እንዲያወግዙ ጠይቀው ድርጊቱን የሚያወግዝ አገር አቀፍ መርሀ ግብር እንዲዘጋጅ አስፈላጊውን ድጋፍ ምክር ቤቱ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በሞጣ ከተማ በመስጊዶች ላይ በደረሰው ጥቃት ሳይረበሽ የተለመደውን የሰላም አምባሳደርነቱን እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።

መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን የሚዲያ ሽፋን በመስጠት እንዲህ አይነት ችግሮች እንዳይባባሱ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ዋና ጸሐፊው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም