ቀጥታ፡

ተማሪዎች ለሃሳብ ልዕልና ተገዥ እንዲሆኑ ምክንያታዊ የሆኑ ክርክሮች ሊዳብሩ ይገባል

ኢዜአ ታህሳስ 12 /2012 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በተማሪዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት በምሁራን የታገዘ የእርስ በርስ የምክክር መድረኮች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

በአሜሪካ ኢምባሲ የበጀት ድጋፍ የሚደረግለት "የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ምክንያታዊ የክርክር ፕሮጀክት" በባህር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ስንታየሁ ገነት በውይይቱ ላይ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት ባህር ዳር ፣ ሃዋሳ ፣ መቀሌን ጨምሮ በ14 ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋመ ነው።

የፕሮጀክቱ ዓላማም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሃሳብ ልዕልና እንዲያምኑና ሀሳብን መስጠትና መቀበልን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ አገር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች መካከል የተከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያታዊነትን ተግባራዊ ካለማድረግና ችግሮችን በውይይት መፍታት ካለመቻል የተነሱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚነሱ ምክንያታዊ ያልሆኑ ግጭቶችን መከላከል የሚቻለው ተማሪዎች በምክንያታዊነት ላይ ተመርኩዘው ሲከራከሩና አንዱ ለሌላው ሀሳብ ተገዥ ሲሆን እንደሆነም አመልክተዋል።

ለዚህም በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ 25 የሚሆኑ ተማሪዎችን አባል በማድረግ ምክንያታዊ የክርክር ክለቦች ተዘጋጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አመልክተዋል።

ዶክተር ስንታየሁ እንዳሉት በምክንያታዊ ክርክሩ የታቀፉ ተማሪዎች ሊያከራክሩ የሚችሉ ሁለት የተለያዩ ተቃራኒ ሃሳቦች ከዩኒቨርሲቲ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡላቸው ሲሆን በክርክሩም የሃሳብ ልዕልናን እንዲያዳብሩና የተሻለውን እንዲቀበሉ ይደረጋል።

"እነዚህ ተማሪዎችም በምክንያታዊ ክርክሩ ያገኟቸውን ሃሳቦች ለሌሎች ጓደኞቻቸው እንዲያጋሩ ይደረጋል" ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ውጤት ማምጣት መጀመሩን የተናገሩት ዶክተር ስንታየሁ፣ ተማሪዎች በሰው ሃሳብ የሚነዱ ሳይሆን በራሳቸው ተማምነው ሞጋች ዜጋ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

"የክርክር መድረኩ ተማሪዎች በመረጃ ላይ ተመስርተው ነገሮችን የሚተነትኑንና ለአፍራሽ ምክንያቶች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ያግዛል" ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል ረዳት መምህርት ወይዘሪት እየሩሳሌም ንጉስ ናቸው።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በስሜት ሳይሆን በሃሳብ እንዲመሩ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክርክር መድረኩ ምክንያታዊ ተማሪዎችን እያፈራ እንደሆነ ገልጸው፣ "በፕሮጀክቱ ሃሳብን ሰጥቶ በመቀበል የሚያምን ተማሪ ማፍራት እየተቻለ ነው" ብለዋል።

"ተማሪዎች ከማንኛውም ወገን የሚነሳን ሃሳብ ሳይመረምሩ በስሜት እንዳይደግፉና እንዳይቃወሙ ፕሮጀክቱ አይነተኛ ሚና ይጫወታል" ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ በላይነህ ዘለቀ ናቸው።

መድረኩ ነገሮችን በመረጃና በማስረጃ አስደግፎ መተንተን የሚችልና ከአሉቧልታ የጸዳ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል።

አቶ በላይነህ እንዳሉት የክርክር ፕሮጀክቱ በአለመስማማት ውስጥ መስማማትን ተቀብሎ የሚኖር ዜጋን ለማፍራት የሚያግዝ ነው።

ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው በእዚህ የውይይት መድረክ በፕሮጀክቱ የታቀፉ ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም