ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ3ሺህ በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል

ኢዜአ ታህሳስ 12 ቀን 2012 በአማራ ክልል ከ3ሺህ በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ክልሉ ለኢንዱስትሪ ልማት ዘርፉ መስፋፋት ባሉት ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ትናንት ተካሂዷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ በላይ ዘለቀ በምክክር መድረኩ ላይ ባቀረቡት ጥናት እንደገለጹት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎችም 2ሺህ 394 አነስተኛ፣ 589 መካከለኛና 123 ደግሞ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ወደሥራ የገቡት ኢንዱስትሪዎችም ከ27ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከ12 ዓመት በፊት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ከ80 ይበልጥ እንዳልነበር ያስታወሱት አቶ በላይ በዚህ ዓመት ቁጥራቸው 3ሺህ 106 መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን፣ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ፣ በብረታ ብረትና እንጨት ምርቶች ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው።

በተያዘው ዓመት በአግሮ ፕሪሰሲንግ ዘርፍ ወደ ሥራ የሚገቡ የምግብ ዘይት፣ የዱቄትና የብስኩት ፋብሪካዎች መኖራቸውን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመው ፋብሪካዎቹ ስራ ሲጀምሩም ከ9ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡

እንደኃላፊው ገለጻ መሬት አጥሮ ማስቀመጥ፣ ለኢንቨስትመንት የተሰጠን ብድር ለሌላ ዓላማ ማዋል፣ ለባንክ እዳ መሬትን ማስያዝና ከቀረጽ ነጻ የገቡ የኢንዱስትሪ ማበረታቻዎችን ለሌላ ዓላማ ማዋል በባለሀብቶች በኩል የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው፡፡

ለአብነትም በክልሉ 243 ባለሀብቶች የተሰጣቸውን የኢንዱስትሪ የግንባታ ቦታ ለረጅም ዓመታት አጥረው አስቀምጠዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው የተሰማሩ ባለሀብቶችም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ የማምረቻ መሳሪያዎችን አለመጠቀም፣ የሰለጠነ ባለሙያ አለማሟላትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር አለመፍጠር ክፍተት ተስተውሎባቸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አማረ በበኩላቸው በዞኑ ከሦስተኛ ወገን ነጻ የሆነ መሬት ባለመዘጋጀቱ ለ9 ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የግንባታ ቦታ ለመስጠት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራር የሆኑት አቶ አማረ ሲሳይ "በከተማው በሳምንት ከ20 በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ ያቀርባሉ" ብለዋል፡፡

በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ምክንያት 16 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ ጠቁመው፣ ሌሎች 208 ባለሀብቶች ደግሞ ለተዘጋጀላቸው ቦታ አፋጣኝ የካሳ ግመታ ባለመከናወኑ ቦታ መረከብ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ባለሀብቶች በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የብድርና የመሬት አቅርቦት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረቶች በዘርፉ የገጠሟቸው ችግሮች በመሆናቸው እንዲፈቱላቸው ጠይቀዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ አንዳንድ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ቀልጣፋ አገልግሎት አለመስጠት እንዲሁም በጉቦና በዘመድ በመስራት ባለሀብቱ የሚደርስበት መጉላላት ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ወደ ክልሉ የሚመጡ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል።

"የክልሉ መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ የአሰራር፣ የመመሪያና የአደረጃጀት ችግሮችን በመፍታት ክልሉ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል" ብለዋል፡፡

በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለበርካታ ሥራ እጥ ወገኖች የሥራ እድል በመፍጠር ወሳኝ ጠቀሜታ ስላላቸው ባለሀብቱ ለሚያነሳቸው ችግሮች በጥናት ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማትና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም