ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰመራ ከተማ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰመራ ከተማ ገቡ
ኢዜአ፤ ታህሳስ 12/2012 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዛሬ ጠዋት ሰመራ ከተማ ገቡ።
ፕሬዚዳንቷ በሰመራ ሎጊያ ከተማ ሱልጣን አሊሚራ ሃንፍሬ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባን ጨምሮ የክልሉ ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሰመራ ሎጊያ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በክልሉ ፖሊስ ማርሽ ባንድ የታገዘ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በሰመራ ከተማ በዛሬው እለት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቀንን አስመልክቶ ከክልሉ አመራሮች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚመክሩም ታውቋል።
ፕሬዚዳንቷ በከተማው በሚኖራቸው ቆይታ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሴት ተማሪዎችንና አመራሮችን ተሳትፎና ከስርአተ-ጾታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩም ተመልክቷል።
ከዚህ ጎን ለጎን የዱብቲ ሪፌራል ሆስፒታልን የሥራ እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም በሰመራ ዩኒቨርስቲና በተመረጡ የከተማው አካባቢዎች ችግኝ ይተክላሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንቷ ብሔራዊ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምክር ቤት ሰብሳቢ መሆናቸው ይታወቃል።