ቀጥታ፡

ህዝቡ የተቃጠሉ ቤተ-እምነቶችን መልሶ በጋራ በመገንባት የቆየውን አብሮነት ለማጎልበት እንዲሰራ ጥሪ ቀረበ

ኢዜአ ታህሳስ 11/2012 መላው ህዝብ በአማራ ክልል ሞጣ ከተማ የተቃጠሉ ቤተ-እምነቶችን መልሶ በጋራ በመገንባት የቆየውን አብሮ የመኖር እሴት የበለጠ ለማጎልበት እንዲሰራ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሞጣ ከተማ ቤተ እምነቶች ላይ የደረሰውን ቃጠሎ በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በኢትዮጵያውያን መካከል ለዘመናት የኖረው ተባብሮና ተፈቃቅሮ የመኖር እሴት እንዲናድ፣ ግጭትና ጥላቻ እንዲፈጠር ለማድረግ ቤተ እምነቶችን በማቃጠል የሃማኖት ግጭት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አላካት ላይ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድም ጉባኤው ጠይቋል። ትናንት ምሽት 12 ሰዓት አካባቢ ሞጣ ከተማ ባሉ የእስልምና እና የኦርቶዶክስ  የእምነት ተቋማት ላይ ቃጠሎ ደርሷል። ይህ ድርጊት የተለያየ እምነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በመከባበርና በመቻቻል ለዘመናት የገነቡትን የአንድነትና ተሳስቦ የመኖር እሴት የሚንድ የጥፋት ተግባር በመሆኑ የሚወገዝ ነው ሲሉ የጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ገልፀዋል። ተግባሩ ዜጎች ለዘመናት የገነቡትን የአብሮነት እሴት የሚንድ፤ በፈጣሪ ዘንድ የሚያስጠይቅ ሃጥያት ጭምር በመሆኑ በዚህ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ሼህ መሀመድ ሲራጅ በበኩላቸው "እምነት ያለው ሰው አዛኝ፣ አሳቢ፤ ለሌሎች የሚጨነቅ መሆኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እምነት ተቋማት፣ አማኒያንና ንብረታቸው ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ከሃይማኖታዊ አስተሳሰብም ሆነ ከሰብዓዊነት የወጣ እኩይ ተግባር ነው ብለዋል። በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊያን "ተከባብሮና ተቻችሎ በመኖር ካዳበርነው እሴቶቻችን በተቃራኒ የሚፈጸሙ ተግባራት በምድር ወንጀል፤ በሰማይ ቤት ደግሞ ሃጥያት መሆናቸውን በመገንዘብ ይገቱ ዘንድ መስራት አለብን፤" ሲሉም አሳስበዋል። በአሁኑ ወቅት "የእምነት አባቶች የሚናገሩት ሰሚ እያጣ ነው" ያሉት ሼህ መሀመድ ወጣቶች ለአባቶቻቸው ክብር መስጠትና ምክራቸውን መስማት አለባቸው ብለዋል። መንግስትም ከህዝቡ ጋር በመተባበር በዚህ የጥፋት ተግባር በተሰማሩ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ህዝቡ በቃጠሎ የተጎዱትን የእምነት ተቋማት በጋራ መልሶ መገንባት አለበት ብለዋል። መንግስትም በድርጊቱ በተሳተፉት ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። ወጣቶች ከስሜታዊነት በመውጣት ለጋራ ሃገራቸው በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም