የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይጀመራል
ኢዜአ ታህሳስ 11/2012 የዘንድሮው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በመጪው ታህሳስ 25 ቀን 2012 በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል። በባለፈው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ በስፖርታዊ ጨዋነት የታዩ ግድፈቶች በዘንድሮው የውድድር ዓመት እንዳይደገሙ ሁሉም አካላት በሃላፊነት መስራት አለባቸውም ተብሏል። የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የቅድመ ውይይት እና እጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ዛሬ በስፖርት ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል። በዚሁ መሰረት ፕሪሚየር ሊጉ ታህሳስ 25 እና 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የዘንድሮው የውድድር ዓመት ታህሳስ 18 እና 19 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲጀመር አሳውቆ ነበር። ነገር ግን ዛሬ በተካሄደው የእጣ ማውጣት ስነ-ስርአት የተወሰኑ ክለቦች 'በጀት ስላልተለቀቀልን መርሃ ግብሩ በአንድ ሳምንት ይራዘምልን'የሚል ጥያቄ አቅርበው ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ውድድሩ በአንድ ሳምንት እንዲራዘም ተደርጓል። በዚሁ መሰረት በመጀመሪያ ሳምንት መርሃ ግብር የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከሊጉ አዲሱ ተሳታፊ ክለብ ሚዛን አማን ጋር ይጫወታል። መከላከያ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ከምባታ ዱራሜ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ቡታጅራ ከተማ ከጎንደር ከተማ እና ፌደራል ፖሊስ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ይጫወታሉ። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ የባለፈው የውድድር ዓመት የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች ጎልተው የታዩበት ነው ብለዋል። ክለቦች ውጤትን በጸጋ አለመቀበል፣ ዳኛን መሳደብና መማታት፣ የደጋፊዎች የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለትና ለህግ ተገዥ አለመሆንና አወዳዳሪ አካላትን ማመናጨቅ በወቅቱ ከታየቱ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይም አሰልጣኞች ህግን በማክበር ደረጃ ክፍተት እንደታየባቸውም ጠቅሰዋል። በተወሰኑ አጋጣሚዎች ዳኞች በተመደቡበት ቦታ አለመገኘት፣ የውሳኔ አሰጣጥ መዛባትና ህግን በአግባቡ የመተርጎም ችግር ባለፈው ዓመት ጨዋታ ከተስተዋሉት ግድፈቶች መካከል ይገኙበታል። እነዚህ ችግሮች ዘንድሮ እንዳይደገሙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት በመስጠት የተቃና የውድድር ጊዜ እንዲኖር መተባበር አለባቸው ብለዋል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሲሳይ ሃይለስላሴ ፌዴሬሽኑ የስፖርታዊ ጨዋነት በሚጥሱ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል። በባለፈው ዓመት በስፖርታዊ ጨዋነት የተወሰዱ ወጥነት የሌላቸውን የውሳኔ አሰጣጦችን በዘንድሮው የውድድር ዓመት ፌዴሬሽኑ እንደሚያርምም አመልክተዋል። ክለቦች ለደጋፊዎቻቸው ስፖርታዊ ጨዋነትን በተመለከተ ትምህርት መስጠት እንዳለባቸውና እንግዳ ክለብን በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ሙሉጌታ ግርማ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሩን ለመፍታት ጣት መቀሳሰር መፍትሔ እንዳልሆነና ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል። ዳኞች የሚፈፅሟቸው ስህተቶች ለስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በር የከፈቱበት አጋጣሚ እንደነበር የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ በዚህ ረገድ ዳኞች በቀጣይ ዓመት ራሳቸውን የማብቃትና ለማሻሻል መስራት እንዳላባቸው አመልክተዋል። የዳኞች ኮሚሽነር ኢንስትራክተር ፈረደ ፍትሀነገስት በበኩላቸው የክለብ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች የስፖርታዊ መርሆዎችን በማክበር ለህግ ተገዢ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም ክለቦች 'ይህ ዳኛ ይመደብልን' ብሎ የመጠየቅ መብት የላቸውም፤ ዳኛ የመመደብ ስልጣን መብት የዳኞች ኮሚቴ ብቻ ነው ብለዋል። በስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የእጅ ኳስ ስፖርት እንዳይቆሽሽ ሁሉም የስፖርቱ ቤተሰብ ከስሜታዊነት በመራቅ በመከባበር፣ በመደማመጥና በመተራረም በጋራ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ተደርጓል። ተሰብሳቢው በተሻሻለው የውድድር ደንብ ላይም ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምጽ አድድቆታል። በ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 ክለቦች ይሳተፋሉ። በባለፈው የውደድር ዓመት ተሳታፊ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ክለቡን ያፈረሰ ሲሆን ሚዛን አማን በዘንድሮው የውድድር ዓመት የሚሳተፍ አዲስ ክለብ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ቡታጅራ ከተማና የፈረሰው ድሬዳዋ ከተማ የውድድር መርሃ ግብሩን ሳይጨርሱ አቋርጠው መውጣታቸው የሚታወስ ነው። የ2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛው የውድድር ዓመት ሲሆን መከላከያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከዚህ በፊት የተካሄዱት ውድድሮች አሸናፊ ናቸው።