ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ የኃይል ስርጭና አገልግሎት ለማሳደግ የመሰረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታዎች እየተካሄዱ ነው

 ኢዜአ ታህሳስ 11 /2012 የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ኃይል ስርጭት ለማሳደግ ከ1ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የመሰረተ ልማት ግንባታና ዝርጋታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። ተቋሙ በአገልግሎቱ አሰጣጥ ዙሪያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በወቅቱ  እንደገለጹት በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በየዓመቱ በአማካኝ በ13 በመቶ እያደገ ነው።

ከፍላጎቱ መጨመር ጋር ተያይዞ የኃይልና አገልግሎት ስርጭቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

የኃይልና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በ500 ከተሞች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና ዝርጋታ ስራዎች  እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል ።

እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል የኤሌክትሪክ ስርጭትና አገልግሎት መስጫ ማእከላት ግንባታ እንዲሁም  የኤሌክትሪክ መስመሮች ዝርጋታ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።

በተጀመሩ ስራዎች አሁን ያለው 59 ነጥብ 5 በመቶ የኤሌክትሪክ አገልግሎትና ስርጭት ሽፋን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 65 በመቶ ከፍ እንደሚል አመላክተዋል ።

ተቋሙ  አሁን ላይ በዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ መስተዳደሮች 28 ዲስትርክቶችና 564 ማዕከላትን በማደረጀት አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።

አገልግሎት አሰጣጡን ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርጉ ዘመናዊ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም  ጠቅሰዋል ።

ከኃይል ፍጆታና አገልግሎት እየተሰበሰበ ያለው ታሪፍ አነስተኛ በመሆኑ የህዝቡን ያቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት አልተቻለም" ያሉት ደግሞ በተቋሙ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው  ናቸው።

አሁን ያለው የአገልግሎት ክፊያ ታሪፍ አነሰተኛ በመሆኑ የግሉ ሴክተር በዘርፉ እንዳይሰማራ ማድረጉንም ተናግረዋል።

"ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ግብዓት ከወጭ የሚገባ በመሆኑ በዘርፉ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ማነቆ ሆኗል" ብለዋል።

የፋይናንስ እጥረት፣የግብዓት አቅርቦት፣የኃይል ብክነትና ስርቆት፣በመሰረተ ልማቱ ላይ የሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች፣የኔትዎርክ ስርጭት  መቆራረጥና የትራንስፎርመር መቃጠል የዘርፉ ተጨማሪ ማነቆዎችና የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ተቋሙ ችግሮቹን ለመፍታት አሰራርን ከማዘመን ባለፈ የአገልግሎት ታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉን ተናግረዋል ።

የመንግስት አቅም የሚጠይቁ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ትብብርና ድጋፍ በማስፈለጉ የምከክር መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈትያ የሱፍ ተቋሙ የደንበኞችን ፍላጎት ማርካት የሚያስችል አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ  እንዳለበት አመልክተዋል ።

"በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፍታትና ለህብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከህግ አውጭው አካልም ሆነ ከመንግስት ተገቢው ድጋፍና እገዛ ያስፈልጋል" ብለዋል ።

ተቋሙ አሰራሩን ለማዘመን ለሚያደረግው የህግ ማሻሻያዎችና ማዕቀፎች ምክር ቤቱ ተገቢውን ዕገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

ለአገልግሎቱ በተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ሰው ሠራሽ  ጉዳቶችን መከላከልና ማስቆም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም