ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በካርቱም እየተወያዩ ነው

ኢዜአ ታህሳስ 11 /2012 የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ በሱዳን ካርቱም ዛሬ ውይይት ጀምረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ውይይቱ በግድቡ የውሃ አሟላልና አጠቃላይ አተገባበር ላይ  ያተኮረ ነው።

በውይይቱ ላይ የአለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባቸው ባለው ግዙፉ የሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የሶስቱ አገራት ባለስልጣናት በግድቡ የቴክኒክ አፈፃፀምና አተገባበር ላይ ሲመክሩ ይህ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፣ የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት በቅርቡ በዋሽንግተን ካካሄዱት ወይይት በኋላ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወስ ነው።

የሶስቱ ሃገራት ሚንስትሮች በዚሁ መግለጫቸው በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ የሁሉንም ፍላጎት በሚያረካ መልኩ በትብብር እና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት አቋማቸውን ገልጸዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹ በውሃ ሚንስትሮች ደረጃ የሚደረግ አራት መንግሥታዊ የቴክኒክ ስብሰባዎችን ለማካሄድ የተስማሙ ሲሆን፤ የዓለም ባንክ እና አሜሪካ ድጋፍ እንዲሰጡ እና በውይይቶቹም በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን በመግለጫው ተመልክቷል።

ሚንስትሮቹ እስከ መጪው ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ከስምምነት ለመድረስ እንደሚሰሩ ነው የተገለፀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም