በአማራ ክልል በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአገሪቱ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የታሰበ ሴራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአገሪቱ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የታሰበ ሴራ ነው
ኢዜአ ታህሳስ 11 /2012 በአማራ ክልል በሞጣ አካባቢ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን ማህበረሰብ ለማጋጨት የተቀነባበረ ሴራ መሆኑ ታውቆ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የሃይማኖት ተቋማቱ ጥሪ አቀረቡ።
ኢዜአ ክስተቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሃይምኖት አባቶችን አነጋግሯል።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ ሼክ ቃሲም ሙሃመድ ታጁዲን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ፅህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ እንዳሉት በሞጣ የተፈፀመው ተግባር ማንንም የማይወክል፣ ከኢትዮጵያዊያን መልካም እሴቶች ያፈነገጠ እኩይ ዓላማ ያላቸው አካላት ሴራ ነው።
በኢትዮጵያ ሙስሊሙና የክርስቲያኑ ማህበረሰብ ለዘመናት አብሮ የኖረና በዝምድናና በደም የተሳሰረ ጭምር መሆኑን የሚናገሩት አባቶቹ ሞጣ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት ግን በሃይማኖት ስም ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ አካላት ድርጊት በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።
ህዝቡ ልክ ባልሆነ መንገድ የእነዚህ አካላት መሳሪያ በመሆን ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳይገባም የሁለቱ ሃይማኖት ተቋማት አባቶች አሳስበዋል።
ይልቁንም መላው ህዝብ በመካከሉ የቆየውን አብሮ የመኖር፣ መተሳሰብና የመረዳዳት እሴት የበለጠ አጠናክሮ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ማጋለጥ እንዳለበትም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአካባቢውና የፌደራል መንግስት አካላትም ጉዳዩን ባስቸኳይ አጣርተው አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ለህዝብ ይፋ ማድረግ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
ወደፊት ተመሳሳይ የጥፋት ተግባራት እንዳይደገሙ የሃይማኖት ተቋማትና መንግስት አብረው ይሰራሉም ብለዋል።