የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች የታገሉት የዜጎች ደም የሚፈስባት አገር ለመፍጠር አይደለም--- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች የታገሉት የዜጎች ደም የሚፈስባት አገር ለመፍጠር አይደለም--- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ
ኢዜአ ታህሳስ 11 / 2012 የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች የታገሉት ለፍትህና እኩልነት እንጂ በእርስ በርስ ግጭት የዜጎች ደም የሚፈስባት አገር ለመፍጠር አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያን በጋራ እንፍጠር" በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደ አገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ላይ ባስተላላፉት መልዕክት ነው።
በአማራና ኦሮሞ ባለሃብቶች ትብብር በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች በጋራ በአፍሪካ ትልቁን ቁጥር ይይዛሉ።
በመሆኑም እነዚህ ህዝቦች የኢትዮጵያን ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር ለአፍሪካውያን አብሮነትም የመስራት ሃላፊነት ጭምር አላቸው ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጭምር በአደባባይ እስከመተቸት የደረሰ ነጻነትን ያጎናፀፈ መብት እንዲመጣ የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች ከፍተኛ ትግል ማካሄዳቸውንም አስታውሰዋል።
የወጣቶቹ ትግል ለፍትህ እና እኩልነት እንጂ በእርስ በርስ ግጭት የሌሎች ተጨማሪ ወጣቶች ደም እንዲፈስ አይደለም ብለዋል።
የሁለቱ ክልል ወጣቶች በመካከላቸው የተፈጠሩ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት የጀመሩትን ጥረት በማድነቅ።
በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች አካበቢ ግጭት በመፍጠር ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ አካላት እንዳሉ መንግስት እንደሚገነዘብም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አብራርተዋል።
በመሆኑም መንግስታቸው የመማር ማስተማር ተግባር የሚከናወንባቸው ቦታዎችን ደህንነት ለመጠበቅ መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከፖለቲካና ፖለቲከኞች በላይ የሆነች ታላቅ አገር ናት ሲሉ ነው የተናገሩት።
"በመሆኑም ሰላምን ፖለቲከኞች ወይም የመንግስት ተቋማት ብቻ እንዲሰጡን መጠበቅ የለብንም" ብለዋል። ሰላም በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ ያለ ልዩ ሃብት መሆኑን በመጠቆም።
እያንዳንዱ ግለሰብ በእጁ ያለውን ሰላም መጠበቅ ከቻለ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ማስቀጠል ቀላሉ የቤት ስራ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሰላም ጉባኤ እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል እንዲሰፋ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራም የሰላም ሚኒስትሯ ቃል ገብተዋል።