ቀጥታ፡

ታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ቀድመው የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

ኢዜአ ታህሳስ 11 / 2012 ታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ አስቀድሞ ለመከላከል የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የታለቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አስገነዘቡ። በኢትዮጵያ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ የሚመክር ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ  እየተካሄደ ነው።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ እንደገለጹት ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ህይወት ዘላቂነትና ሀገሪቱ ህዳሴ ጉዞ መረጋገጥ በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ የውሃ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ መከላከል ይገባል።

በተለይም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በገንዘብ፣በጉልበትና በእውቀት ያደረገው አስተዋጽኦ አነስተኛ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ግድቡ በደለል እንዳይሞላ አስቀድሞ ለመከላከል በሁሉም አቅጣጫ የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በሁሉም አካባቢ ለተፋሰስ ልማት ስራዎች በተሰጠው ትኩረት 81 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ስራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል።

ግድቡ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረውን ጉልህ ሚና መወጣት እንዲችል ከወዲሁ ግድቡን ከደለል ሙላት ለመታደግ የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ሰራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ የኢትዮጵያ  ህዝቦች አንድነትና መተባበርን በተግባር ያረጋገጠው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ 69 ነጥብ 7 በመቶ ደረጃ ላይ ደርሷል።

"በትግራይ ክልል በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሰራዎች ግድቦች በደለል እንዳይሞሉና ለም አፈራችንን በጎርፍ ታጥቦ  እንዳይሄድ ያበረከቱት አስተዋጾ ከፍተኛ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ ናቸው።

 በክልሉ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ስራዎች 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአረንጓዴ ልማት መሸፈኑን ጠቅሰዋል ።

ይህም በክልሉ 3 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል አስተዋጾ ማድረጉን አመልክተው  በክልሉ የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ሰራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

ለሶስተኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ  በኢትዮጵያ በውሃ ግድቦችና በተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ ያተኮሩ  አምስት ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።

በውይይት መድረኩ  የተፋሰስ ልማት ሞዴል አርሶ አደሮች፣የፌዴራልና የክልሎች አመራሮች፣ ምሁራን፣ የኃይማኖት መሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ነው።

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን እንደርታ ወረዳ በመካሄድ ላይ ያሉ ሞዴል የተፋሰስ ልማት ስራዎች ጉብኝት እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም