አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ድጋፍ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ድጋፍ አጸደቀ
ታህሳስ 11/2012 አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ በሶስት ዓመት የሚተገበር 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ድጋፍ ማፅደቁን አስታውቋል።
ቦርዱ ያፀደቀው የገንዘብ ድጋፉ አገሪቱ የነደፈችውን አገር በቀል የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ መርሃ ግብር ለመተግበር የሚውል ነው ተብሏል። ተቋሙ በድረ-ገጹ እንዳስታወቀው እገዛው የአገሪቱን ማክሮ ኢኮኖሚና የህዝቦቿን ኑሮ ለማሻሻል ከፍተኛ እገዛ ያበረክታል።
በቦርድ አባላቱ ውሳኔ መሰረት 308 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላሩ በአስቸኳይ ለአገሪቱ ይለቀቃል።
የቦርድ አባላት ውይይት መጠናቀቅን ተከትሎ የተቋሙ ተቀዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ተጠባባቂ ሊቀመንበር ዴቪድ ሊፕቶን እንደተናገሩት "በጠንካራ ፖሊሲ የተደገፈው የኢትዮጵያ ልማት ጉዞ ለአስርት አመታት የዘለቀ ፈጣን እድገት ለማስመዝገብ አስችሏል፤ በዚህም ድህነትን ከመቀነስ ባለፈ የህዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ተችሏል"
ነገር ግን በመንግስት ኢንቨስትመንት ታግዞ የሚከናወነው ይህ እድገት የራሱ ውስንነት አለበት ያሉት ሊፕቶን መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛን ለማስተካከል፣ የውጭ የብድር ጫናን ለመቀነስ፣ የገንዘብ ጉድለትን ለመድፈንና በግል ባለሃብት የሚመራ እድገት እንዲኖር መሰረት ለመጣል አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሸያ ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመከላከል፣ የውጭ እዳን ለማመጣጠን፣በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ የንግድ ተቋማትን ለግል ባለሃብት ለማስተላለፍ የተያዘውን እቅድ ለመደገፍ፣ የፋይናንስ መረጋጋትን ለማስፈንና የውስጥ ገቢ አሰባሰቡን ለማዘመን የሚያግዝ ነውም ብለዋል።
እንዲሁም የገንዘበ ቁጥጥሩን በማጥበቅ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል፣ለግሉ ዘርፍ የብድር አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግና ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት ያስችላልም ሲሉ የአይኤምኤፍ ተቀዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ተጠባባቂ ሊቀመንበር ዴቪድ ሊፕቶን ገልፀዋል።
ሰፋ ያለ የገንዘብ ምንዛሪ ዝውውር እንዲኖር ለማድረግ በጠንካራ የቁጥጥር ፖሊሲ መደገፍ አለበት የሚሉት ዴቪድ ሊፕቶን በዚህም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል፤በተጨማሪ በመንግስትና በተጓዳኝ ያለውን የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ማስቀረት ይቻላል ሲሉም ገልፀዋል።
ለውጡን በጠንካራ የባለቤትነት ስሜትና በሙሉ አቅም መተግበር ከተቻለ መንግስት የያዘው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያለጥርጥር የማክሮ ኢኮኖሚውን ደረጃ በማሻሻል የውጭ ብድር ሰለባ ከመሆን ያላቅቃል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስረድተዋል።
በፕሮግራሙ ቅድሚያ የሚሰጠው የግል ባለሃብቱን የኢንቨስትመንት አቅርቦት ጥያቄ መመለስና የንግድ ከባቢ ሁኔታውን ማሻሻል ሲሆን በዚህ በመታገዝ የግል ባለሃብቱ የሚመራው የኢኮኖሚ እድገት እንዲፈጠር ያስችላል" በማለት ሃላፊው ጠቅሰዋል።