ቀጥታ፡

ባህልን በአግባቡ ጠብቆ ማሳደግ ለቱሪዝም ልማትና ለህዝቦች ትስስር ሚናው የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

ኢዜአ ታህሳስ 10 / 2012 ---የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል በአግባቡ ጠብቆ ማሳደግ ለቱሪዝም ልማትና ለህዝቦች ትስስር ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ  ማህበረሰብ 10ኛውን የቱሪዝም ሳምንት በዓል “ቱሪዝም ለባህል ማንሰራራት” በሚል  መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል። በበዓሉ ላይ "የባህል ምንነት፣ ልማትና ጠቀሜታው" በሚል ርዕስ በቋንቋና ባህል ምሁሩ ዶክተር ኃይለሚካኤል አበራ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል። በእዚህ ወቅት ዶክተር ኃይለሚካኤል እንዳሉት ባህል ልንጠብቀው፣ ልናሳድገውና ለልማት ልናውለው የሚገባ የዜጎች የህልውና እና የማንነት መሰረት ነው። ባህል የአንድ አካባቢ ማህበረሰብ ልምድ፣ አመጋገብ፣ አለባበስ እና ታሪክ መገለጫ መሆኑንም ጠቁመዋል። በማህበረሰቡ የሚደረጉ እና የተከለከሉ ተግባራትን ከመለየት ባለፈ የአንድ ማህበረሰብ ወግ፣ ልማድ፣ ደንብና ህግን አቅፎ የያዘ ያልተጻፈ ህገመንግስት መሆኑንም አመልክተዋል። እንደ ዶክተር ኃይለሚካኤል ገለጻ ኢትዮጵያውያን በባህልና በታሪክ እሴቶች አንድነታቸውን አስጠብቀው በመከባበር እና በመቻቻል እስከዛሬ ድረስ ቆይተዋል። "ባህል ለህዝብ ለህዝብ ትስስር እና ለቱሪዝም እድገትና ልማት ያለው ትልቅ ፋይዳ በመገንዘብ  ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ይገባል" ብለዋል። በመሆኑም በአገሪቱ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል በአግባቡ ጠብቆ ማሳደግ ለቱሪዝም ልማትና ለህዝቦች ትስስር ሚናው ከፍተኛ መሆኑ አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የህዝቦችን ባህል የጋራ እሴቶች ማክበርና ጠብቆ ማቆየት ቀጣይነት ያለው ልማት ለማካሄድ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ዶክተር ኃይለሚካኤል እንዳሉት የባህል ጥቃትን ከመከላከል ጎን ለጎን ባህል ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፣ ለልማት እና ማህበራዊ ግንኙነት ያለውን ጥቅም ከታች ጀምሮ ማስተማር ይገባል። "ወጣቶችም ባህላቸውን በሚገባ አውቀውና ጠብቀው  ለትውልድ የሚያስተላልፉ መሆን  ይኖርባቸዋል" ብለዋል ። በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም እና አርኪዮሎጂ ኢንስቲዩቲት ዳይሬክተር አቶ ተክለብርሃን ለገሰ በበኩላቸው በተቋሙ በየዓመቱ የቱሪዝም ሳምንት እንደሚከበር ገልጸዋል። ይህም ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው ማህበረሰብ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህሎችና ቅርሶችን እንዲያውቅ እና ከቱሪዝም ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነቱ እንዲጠናከር ማገዙን ነው ተናግረዋል። "የበዓሉ መከበር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ታሪክ፣ ባህል እና ቅርስ በፎቶ ዓውደ ርዕይ ጭምር በማቅረብ ተማሪዎች ለሰላምና አንድነተት እንዲቆሙ ያግዛል" ብለዋል። ተማሪዎች በባህል ልውውጥ ግንኙነታቸው እንዲያጠናክሩ ትልቅ ሚና እንዳለውም ነው ዳይሬክተሩ የጠቆሙት። "የበዓሉ መከበር የዩኒቨርሲቲውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማቀራረብ በቅርሶች ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ እንዲያዝ ያደርጋል" ያለችው ደግሞ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ማናጅመንት የሦስትኛ ዓመት ተማሪ ግደይ ገብረእግዚአብሔር ናት። "በዓሉ በአገሪቱ ያሉ ቅርሶች እና የተለያዩ ህዝቦችን ባህል እንድናውቅ እና በመካከላችን ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር ፋይዳው የጎላ ነው'' ብላለች። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከትምህርት ጎን ለጎን የታሪክና የባህል ልውውጥ በማድረግ በልዩነት ውስጥ  አንድነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸው የገለጸው ደገሞ የሦስተኛ ዓመት የቱሪዝም ተማሪ ሙባረክ ተሾመ ነው። የቱሪዝም ሳምንት በዓሉ በጽዳት ዘመቻ፣ በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችና በውዝዋዜ ውድድር እንዲሁም በፎቶ ዓውደ ርዕይና በውይት ለአምስት ቀናት በድምቀት ተከብሯል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም