ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች አካል የሆነውን ጥምረት 8 ነጥብ 7ን በጋራ መተግበር የሚያስችላትን መርሃ ግብር ይፋ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች አካል የሆነውን ጥምረት 8 ነጥብ 7ን በጋራ መተግበር የሚያስችላትን መርሃ ግብር ይፋ አደረገች
ኢዜአ፤ ታህሳስ 10/2012 ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች አካል የሆነውን ጥምረት 8 ነጥብ 7 በመባል የተገለጸውን ሰዎችን በጉልበት ስራ ማሰማራት፣ ዘመናዊ ባርነት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቀረት የሚያስችለውን ትብብር ይፋ እድርጋለች።
የሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር ዛሬ ግቡን ይፋ በማድረግ በስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዝግጅት ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ''ኢትዮጵያ ሰውን ማዕከል ያደረገ ለውጥና ልማት እየተገበረች ትገኛለች'' ብለዋል።
አቶ ደመቀ እንዳሉት፤ ሰውን መሰረት ያደረገ ልማትና ሰውን ያከበረ ልማት ምን ጊዜም ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው።
በዚሁ መሰረት የዘላቂ ልማት ግቦች አካል የሆነው ይህ ግብ ሕጻናትንና ታዳጊዎችን ከአደጋ መታደግ የሚያስችል መሆኑ መታወቅ እዳለበት አስገንዝበዋል።
የዘላቂ ልማት ግቡ በአንድ አካል ጥረት የሚሳካ ሳይሆን በሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ መሆኑን የዘርፉ ተዋናዮች ሊረዱት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
''በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ችግር በመቅረፍ በአፍሪካና ለተቀረው ዓለም ምሳሌ የሚሆን ተግባር ይፈጽማል'' ብለዋል።
እስካሁንም ሕጻናትና ታዳጊዎችን ለመታደግ ከተዘጋጁ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ከአጀንዳ 2063 ዓ.ም ጋር ተናቦ እንዲተገበርም እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የዘላቂ ልማት ግቡ በፍጥነት ይሳካ ዘንድ በትብብር የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በቀዳሚ አጋርነት ኃላፊነቱን ወስዳ መንቀሳቀሷ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትሯ፤ መንግስት ቀደም ብሎ ችግሩን ለመግታት ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ ተናግረዋል።
ከነዚህ ጥረቶች መካከል አገሪቷ በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅትና በመንግስታቱ ድርጅት የተዘጋጁ ስምምነቶችን ቀድማ በማጽደቅ እየተገበረች ትገኛለች።
''በተጨማሪም ብሔራዊ የትግበራ መርሃግብር ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ሲሆን የሕገወጥ ሰዎች ዝውውርና በሰዎች መነገድ ወንጀል ተከላካይ ብሔራዊ ምክር ቤት በፌዴራል ደረጃ ተቋቁሞ እየሰራ ነው'' ብለዋል።
ይህም ሆኖ አሁንም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ''የጋራ ጥረቶች ከምንም ጊዜ በላይ መጠንከር አለባቸው'' ብለዋል።
እ.አ.አ በ2015 በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ 43 በመቶ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 7 ዓመት የሆኑ ሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ ሰለባ መሆናቸውን በአብነት ጠቅሰዋል።
ፖሊሲ አውጪዎች፣ ቀጣሪዎች፣ የንግድ ማህበራት፣ የሕብረተሰብ መሪዎችና መገናኛ ብዙሃን ተናበው እንዲሰሩ ዶክተር ኤርጎጌ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የሰራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽኖችና የንግድ ማሕበር ኃላፊዎች ችግሩን ለመከላከል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በዓለም ላይ ከ152 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትና ታዳጊዎች ለጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የዘመናዊ ባርነት ሰለባ የሚሆኑ ሲሆን 25 ሚሊዮን ሰዎች በግድ ስራ ላይ እንዲሰማሩና 15 ሚሊዮን ደግሞ በግድ እንዲያገቡ ይደረጋል።
ተመድ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ለ15 ዓመታት እየተተገበረ በሚገኘው የዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶቷል።
መርሃ ግብሩ ከጉልበት ብዝበዛው በተጨማሪ ህጻናት ለውትድርና አገልግሎት እንዳይዉሉ የማድረግ ግብም አካቷል።