ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ውሳኔ መተላለፉ የአገሪቱን የቱሪስት ፍሰት ይጨምረዋል

ኢዜአ፤ታህሳስ 10/2012 በኢትዮጵያ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ አገራዊ የቱሪስት ፍሰትን እንደሚጨምርና የቱሪዝም ዘርፉን እንደሚያነቃቃ ተገለጸ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው ጥምቀት ካህናት፣ ቀሳውስት፣ የሰንበት ተማሪዎች፣ ህጻናት፣ አዛውንትና ሌሎችም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በአደባባይ ወጥተው በአሉን በታላቅ ድምቀት ያከብሩታል። በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘቱን ሳይለቅ ታቦታቱ በዝማሬና ታጅበው ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ አምርተው ያድራሉ። ይህም የሚደረገው ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱን ምሳሌ ምክንያት በማድረግ መሆኑንም የመጽሃፍ ቅዱስ ድርሳናት ያስረዳሉ። ይህ ሃይማኖታዊ በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ቀልብ እየሳበ በመምጣቱ የአከባበር ሥነ-ስርዓቱን በዩኔስኮ ጥበቃ ስር በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። የአለም ቅርሶችን እያጠና በሚዳሰሱና በማይዳሰሱ ዘርፎች መዝግቦ እውቅና የሚሰጠው ዩኔስኮ ታህሳስ 1 ቀን 2012 ዓ.ም በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ በተደረገ ስብሰባ ላይ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ጥምቀትን ጨምሮ አምስት የአለም ባህላዊ ቅርሶችን "በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት" በማይዳሰሱ የአለም ቅርሶች መዝገብ ላይ እንዲፍሩ የውሳኔ ሃሳብ ተላልፏል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የመስቀል ደመራ በዓል፣ የገዳ ስርዓትንና የፊቼ ጫንበላላ በዓልን በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ማድረግ ችላለች። የጥምቀት በዓልን ለማስመዝገብ በተደረገው ጥረት ጂቡቲ፣ ሴኔጋል፣ ቶጎ፣ ሞሪሺየስ፣ ካሜሮን፣ ዛምቢያ፣ ኩዌት፣ ፍልስጤም፣ አዘርባጃን፣ አርሜኒያ፣ ቻይና፣ ፖላንድ፣ ሊባኖን፣ ጃማይካ፣ ቆጵሮስ እና ኩባ የድጋፍ ድምጻቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአሉ የአለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ትልቁን ድርሻ ተወጥታለች ሲሉ የቤተክርስቲያኗ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብጹእ አቡነ አረጋዊ (ዶክተር) ገልጸዋል። በተለይም በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር በህዝቦች መካከል ማህበራዊ ትስስርን እያጠናከረ ባህልንና ወግን እያዳበረ የመጣ መሆኑንም አመልክተዋል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ እንደገና ደሳለኝ በበኩላቸው በዓሉ በዩኔስኮ ሲመዘገብ የአገሪቱን የቱሪስት መስህብነት የበለጠ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል። ''በዚህም በጥምቀት በአል አከባበር ላይ ከዚህ ቀደም ወደ አገር ውስጥ ይመጣ የነበረውን የቱሪስት ቁጥርም በተሻለ ሁኔታ ይጨምራል ነው'' ያሉት። እንደጥምቀት በዓል ያሉ የአደባባይ በአላት የአገር ገጽታን ለመገንባትና ሰላምን ለመስበክ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም የተናገሩት አቶ እንደገና፤ የአገሪቱን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያነቃቃ መሆኑን አመልክተዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የባህል ተመራማሪ አቶ ገዛኸኝ ግርማ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በርካታ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል። ''ቅርሱን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍና የእውቀትና ሽግግር እንዲኖረም ያደርጋል'' ብለዋል። በበአሉ ላይ የሚንጸባረቁ የተለያዩ የአለባበስና ሌሎች ባህሎችና እሴቶችንም ለአለም ህብረተሰብ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል። አገሪቱ ከቱሪዝም ሃብት የበለጠ የምትጠቀምበትን እድል በማመቻቸት ብሎም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ፋይዳዎች ተጠናክሮ እንዲሄዱ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም አብራርተዋል። በመሆኑም ህዝቡ የጥምቀት በዓል አላማውን ሳይስት ከትውልድ ትውልድ ተጠብቆ እንዲተላለፍ በማድረግ ረገድ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ጥሪ ቀርቧል። በ2010 ዓ.ም. የጥምቀት በአል ላይ ብቻ 15 ሺህ የተለያዩ አገሮች ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም