ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሳተላይት መምጠቅ የፈጠራ ሥራቸውን ለማጎልበት ተነሳሽነታቸው እንደሚጨምር ተማሪዎች ተናገሩ

ኢዜአ ታህሳስ 10/2012ኢትዮጵያ ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ የፈጠራ ሥራና የምርምር አቅማቸውን ለማጎልበት ተነሳሽነታቸው እንደሚጨምር ልዩ ተሰጦ ያላቸው የአዳማ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ገለጹ። ተማሪዎቹ ይህንን የገለጹት በአዳማ ሳይንስቴና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ  የሂሳብ፣ሳይንስ፣ኢንጅነርንግና ቴክኖሎጂ ማዕከል በመገኘት ኢትዮጵያ ዛሬ ወደ ህዋ ያመጠቀችው ሳተላይት ሂደት በቀጥታ የቴሌቭዥን ሰርጭት በተከታተሉበት ወቅት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ነው።

የአስረኛ  ክፍል ተማሪ ዮሐንስ እንዳሻው እንዳለው ኢትዮጵያ  ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ በፈጠራ ያላቸውን ልዩ ተሰጦና የምርምር ሥራቸውን እንዲያጎለብቱ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል።

የፈጠራ ሥራችን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ  ተነሳሽነታቸው እንደሚጨምር ገልጾ ለዚህም መሳካት የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ  የሚናከናውነው የፈጠራ ሥራን ለማዳበር የቤተ ሙከራ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናገሯል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ተልዕኮ የሚፈፅም ሮቦት ለመፍጠርና ችግር ፈቺ  ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሷል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሰርካልም ደለለኝ በበኩሏ "ሀገራችን የአካባቢዋን አየር ንብረት፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን በራሷ አቅም ለመቆጣጠር ሳተላይት ማምጠቋ ተደስቼያለሁ፤ ኮርቼያለሁ" ብላለች።

የጠፈር ምርምር ማዕከል እንጦጦ ላይ መከፈቱ   የምርምርና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን  ለማዳበር አቅም እንደሚፈጥራላቸውም ገልጻለች።

ተማሪዋ እንዳለችው ከውጭ የሚገቡ የተንቀሳቃሽ የኤሌክትሮኖክስ መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችል የምርምር ሥራዎች  እያከናወነች ነው።

በዚህ ላይ ኢትዮጵያ ሳይተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ ለሀገሯ  የተሻለ ቴክኖሎጂ ለማበርከት የሚያስችል ዕውቀት፣አቅምና ክህሎት ለመቅሰም ተነሳሽነት እንደሚጨምር ተናግራለች።

"ሀገራችን የራሷ የሆነ ሳተላይት ወደ ህዋ መላኳ ኢትዮጵያ  በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስክ  የመጀመረችውን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ከማገዝ አንፃር ትልቅ ፋይዳ አለው" ያለው ደግሞ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ነው።

በቀጣይነት ሀገሪቱ  በራሷ ሙያተኞች ሳተላይት ግንብታ ማምጠቅ እንዲትችል ተስፋ የሚሰጥ እንደሚሰጥ  የገለጸው ተማሪ ቴዎድሮስ "የህዋ ሳይንስ የምርምር ማዕከል ብቃት ባላቸው የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ በማጠናከር ላይ በትኩረት መሰራት አለበት "ብለዋል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ  የሂሳብ፣ሳይንስ፣ኢንጅነርንግና ቴክኖሎጂ ማዕከል ኃላፊ ዶክተር አማን ደቀቦ በበኩላቸው "ሀገሪቷ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቋ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ የሚያስችል ከመሆኑም ባለፈ የሞራል ስንቅ ጭምር ይሆናቸዋል" ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ  ዘርፍ ያለባትን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት   የሂሳብ፣ኢንጂነሪንግ፣ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጥናትና ምርምር ማዕከል እያደረጃ መሆኑንም  ገልጸዋል።

ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አቅማቸውን ለማዳበር በጥናትና ምርምር ዘርፍ  በዩኒቨርሲቲው የቤተ ሙከራ  አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም