ቀጥታ፡

ለዛሬው አንድነትና ፍቅር ህይወታቸውን የገበሩ ሰማእታትን ልናከብር ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010ለዛሬው አንድነትና ፍቅር ህይወታቸውን የገበሩ ሰማእታትን ልናከብር ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት  እሳቸው ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ላመጧቸው ለውጦች ድጋፍና እውቅና መስጠትን ዓላማ አድርጎ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው ሰልፍ ላይ ነው። በንግግራቸውም የህዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ ህይወታቸውን የገበሩ ሰማእታት ለአሁኗ ኢትዮጵያ መሰረት ናቸው ሲሉ ተናግራዋል። በአሁኑ ወቅትም አገሪቱ በፍቅርና በአንድነት በተለይም በአብሮነት መንፈስ በመተጋገዝ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቤት ስራ ነው ብለዋል። የእምነት አባቶች ሙስናንና ዘረኝነትን ለማስቆም  ኃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የቀደመውን ቂምና በቀል ወደ ኋላ በመተው ለኢትዮጵያ እድገት በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል። ወጣቱ ትውልድ ሌብነትንና የዜጎችን መበታተን በመጠየፍ የአገርን ፍቅር በማሳየት እኩልነትን የሚሰብክ ትውልድ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል። በተለይም ከአመራሩ ጎን በመቆም በሁሉም ዘርፎች ላይ ያላቸውን ሚና በማጎልበት አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የወጣቱ ሚና የጎላ በመሆኑ ሁሉም ወጣት ይህንን ተግባሩን እንዲያጠናክር አሳስበዋል። በዋናነትም ዘረኝነትንና የክልል ወሰኖች ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በጋራ በመግታት የዜጎችን መፈናቀል በማስቆም ወጣቱ ትልቁን ድርሻ ሊወስድ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተናግረዋል። በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መጥተው ከዜጎቻቸው ጋር በመደመር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማደረስ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያወርሱት የኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስም አንድነትንና ፍቅርን እንዲሁም መንግስት ቤተመንግስቱም ሆነ ፓርላማው ለህዝቡ ክፍት የሚሆንበት ቀን መምጣት አለበትም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌብነትና ከዘረኝነት በነጻ መንፈስ ህዝቡን እንደሚያገለግሉም ቃል ገብተዋል። ኃላፊነትን ከተረከቡ መንፈቅን እንኳን ሳያስቆጥሩ ህዝብ እሳቸውን ለመደገፍ ባደረገው ርብርብም ህዝቡን ምስጋናና አክብሮት ችረዋል። ''የዛሬው የፍቅርና የአንድነት ቀን መድረስ ከሚገባን የፍቅር ማማ የመጀመሪያው ጡብ መቀመጡን ያሳያል'' ሲሉ የዛሬዋን ቀን አወድሰዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም