ቀጥታ፡

የሠላም ሚኒስቴር በሠላም እሴት ግንባታ ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ይሰራል

ኢዜአ፤ታህሳስ 9/2012 በሠላም እሴት ግንባታና በግጭት አፈታት ዙሪያ ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ የሠላም ሚኒስቴር አስታወቀ። በአገሪቷ የሚገኙ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ማኅበራት በሠላም ግንባታና ግጭት ማስወገድ ያላቸው ሚና በሚል ዛሬ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ውይይት ተካሂዷል። የሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታ ዳይሬክተር ዶክተር ራህዋ ሁሴን እንዳሉት ሚኒስቴሩ በሠላም ግንባታ ዙሪያ ከማኀበራቱ ጋር በቅርበት መስራት ይፈልጋል። ዘላቂ ሠላም ለማምጣትና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረትም የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል። ማኅበራቱም ካላቸው ተደራሽነትና ህብረተሰቡን በቅርበት ከማግኘት አንጻር ስለ ሠላም በሚሰሩ ስራዎች የቅርብ አጋሮች ናቸው ብለዋል። አሁን የያዙት ዓላማ መንግስት ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ከጀመረው ተግባር ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የሠላም ሚኒስቴር ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት። የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማኅበር ኅብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ለገሰም የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ግጭቶች እንዳይከሰቱና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መስራት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ። በተለይም የህግ የበላይነት እንዲከበርና ዜጎች ህይወትና ክብራቸውን እንዳያጡ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። የሲቪክ ማኅበራቱ እንዲተባበሩና ፈጣን ተግባር እንዲያከናውኑም ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል። ውይይቱ ዓላማም ማኅበራቱና ድርጅቶቹ አገሪቷ ባለችበት ሁኔታ የጋራ አቋም ለመያዝ፣ የሠላም ግንባታና የግጭት አወጋገድ ዙሪያም የመፍትሄ ሃሳብ ለማስቀመጥ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው በአገሪቷ የሠላምና የልማት ስራዎችን ተደራሽነት ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሲቪክ ማኅበራት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በአዋጅ የተሰጣቸውን መብት በተግባር ተርጉመው ማሳየት ይገባቸዋልም ብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ ማኅበራቱ የግጭት አፈታት እሴቶች እንዲጎለብቱና አገሪቷ እያስተናገደችው ያለው የሠላም እጦት እንዲጠፋ ብርቱ ጥረት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማኅበር ኅብረት ከተለያዩ አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ውይይት ከ3 ሺህ በላይ የማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም