ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተወሳሰቡ የመጡ ችግሮች ከወዲሁ ካልተገቱ 'መጪው ትውልድ ችግር ወራሽ ይሆናል' ሲሉ ምሁራን አሳሰቡ

ታህሳስ 9/2012  በኢትዮጵያ ያልተፈቱና ዘመኑ ፈጥሯቸው እየተወሳሰቡ የመጡ ችግሮች ከወዲሁ ካልተገቱ 'መጪው ትውልድ ችግር ወራሽ ይሆናል' ሲሉ ምሁራን አሳሰቡ።

ከተለያዩ የሙያ ማሕበራት የተውጣጡ በርካታ ምሁራንና ሌሎች የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሯል።

ለመጪዎቹ ሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባኤው ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ እስከ 2050 ሊገጥሟት የሚችሉ ተግዳሮቶችና ዕድሎች ዙሪያ በመምከር ላይ ነው።

በጉባኤው ላይ በአገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች የተዘጋጁ ፅሁፎች ይቀርባሉ፤ ውይይትም ይደረግባቸዋል።

በኢትዮጵያ የሚስተዋሉት ተግዳሮቶች በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ መልክን የተላበሱ ቢመስሉም አገሪቱ ዘመኑ የፈጠራቸው ሁሉን አቀፍ ችግሮችም የሚታዩባት ናት።

በጉባኤው ላይ የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዋ ዶክተር ደብረወርቅ ዘውዴ በሕዝብ ብዛትና ተያያዥ ምክንያቶች ኢትዮጵያ እየገጠማት ያሉ ችግሮችና ዕድሎችን  አብራርተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ በኢትዮያ 44 በመቶ ያህሉ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ሲሆን 78 በመቶ ያህሉ ደግሞ ገቢው በቀን ከ2 ዶላር ያነሰ ነው።

አለፍ ሲልም ከ70 በመቶ በላይ ሕዝቦቿ ኤሌክትሪክ የማያገኙ፣ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት፣ የመጸዳጃና የፍሳሽ አወጋገድ ችግር እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በተቀራኒው ደግሞ የሕዝብ ቁጥሩ በዚው ከቀጠለ በአውሮፓዊያኑ 2050 የአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ወደ200 ሚሊዬን ገዳማ ሊያሻቅም እንደሚችል ይገመታል ነው ያሉት ባለሙያዋ።

''መፍትሔው ችግሩን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ነው'' የሚሉት ዶክተር ደብረወርቅ 'የሚሰራውን የወጣት ጉልበት ወደ ኢንቨስትመንት ማስገባት ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ከዚህ ጎንለ ጎን ሙስናን መግታት፣ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን ማሻሻል፣ ውጤታማ ኢንቨስትመንት ፖሊሲ መተግበርና መልካም አስትዳደርን ማረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ሌላው ከአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ሊገጥሟት የሚችሉ ነባራዊ ሁኔታና መልካም ዕደሎችን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት ደግሞ የምህንድስና ባለሙያው ፕሮፌሰር አስፋው በየነ ናቸው።

ያደጉ አገራት ባደረሱት አካባቢያዊ ተጽዕኖ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ አገራት ለከፍተኛ ስጋት መዳረጋቸውን ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።

ለአብነትም ዓለም በ1900 ዓ.ም 20 ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ያስተናገደች ሲሆን ይህ አኃዝ በ2006 ወደ 300 አሻቅቧል፤ ይህ እጅግ አሳሳቢ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አገር ከስጋት ለማምለጥ ግብርናዋን ከዝናብ ማላቀቅ፣ አካባቢን መጠበቅና ተግበራዊ ሊደረግ የሚች ፖሊሲ መተግበር ያስፈልጋታል ነው ያሉት።

በጉባኤው ላይ የታደሙት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለም በኢትዮጵያ የውኃ ኃብትና መስኖ ልማት ላይ የተደቀኑ ስጋቶችን በተመለከተ ፅሁፍ አቅርበዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በጥቅሉ ግጭት፣ ድህነት፣ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችና የአየር ንብረት ለውጥ የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው።

በተለይ ደግሞ በዘርፉ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ያለመኖር፣ አብዛኞቹ ወንዞች ድንበር ተሻጋሪ መሆናቸው፣ የመሬት ማራቆትና ኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ ችግሩን አወሳስቦታል ብለዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም መንግስት እነዚህን ችግሮች መቀነስ የሚያስችሉ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ እውጥቶ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበሉላቸው መንግስት ሁሉን አቀፍ ችግሮቹን ቀድሞ ተረድቶ ዘላቂ መፍትሔዎችን እያበጀ ይገኛል ብለዋል።

ከነዚህ መካከል የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሸያ፣ ትላልቅ የንግድ ስራዎች ላይ የግሉን ዘርፍ የማሳተፍ እንዲሁም ኢንቭስትመንትን የሚያቀሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚሁ አጋጣሚ የትራንስፖርት ዘፉን ማዘመን የሚያስችል ሃሳብ ያላቸው ምሁራን ከሚኒስቴሩ ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ሌሎች የምክክሩ ገለጻ አቅራቢዎችም እየመጣ ያለው ችግር በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን ገልጸው ከምንም በላይ ለዘመናዊ እርሻ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ጉባኤውን በዋናነት የኢትዮጵያ ኢንጂኒየሮች የጋራ ማሕበራት ጥመረት፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበርና የአርክቴክቶች ማህበር አዘጋጅተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም