ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ጉባዔ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራን የሚደግፉ ስምምነቶች አድርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ጉባዔ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራን የሚደግፉ ስምምነቶች አድርጋለች
ኢዜአ፤ ታህሳስ 9/2012 ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአየር ንብረት ለውጥና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራ መደገፍ የሚያስችሉ ስምምነቶች ማድርጓን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ። ስምምነቶቹ በስፔን ማድሪድ በተካሄደው 25ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በተደረጉ የሁለትዮሽና የጎንዮሽ ውይይቶች እንደሆነ በጉባኤው የተሳተፈው ኮሚሽኑ በዛሬ መግለጫው አስታውቋል። የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንዳሉት ከጉባዔው ጎን ለጎን የአየር ንብረት ለውጥ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ትግበራን መደገፍ የሚያስችሉ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎች እንድታገኝ የሁለትዮሽ ምክክሮች ተካሂደዋል። በዚሁ መሰረትም ለኢትዮጵያ አረጓዴ ልማት ትግበራ ድጋፍ ለሚያደርጉ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች 50 የሚጠጉ የሁለትዮሽና የጎንዮሽ ውይይቶችና ገለፃዎች ተደርገዋል። ገለፃ የተደረገላቸው አገራትና ተቋማት ነባሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ አዳዲሶች ደግሞ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ከስምምነት ተደርሷል። የእንግሊዝ መንግስት ሌሎች አገራትን ጨምሮ ለኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ማሻሻያ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የስምምነት ሰነድ መፈረሙን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የኔዘርላንድ መንግስት ከዚህ ቀደም እያደረገ ካለው ድጋፍ በተጨማሪ ከግብርና ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ትግበራ አንጻር የተከናወኑ ስራዎችን ማጠናከር የሚያስችል ድጋፍ እንደሚሰጥ አሳውቋል። የዘንድሮው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በዋናነት የፓሪሱ ስምምነትን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ድርድር ላይ ያለውን መመሪያ በማጠናቀቅ እ.አ.አ 2020 ይኸው ስምምነት መተግበር የሚጀምርበት ነበር። እንዲሁም አገራቱ ስምምነቱን ተግበራዊ ለማድርግ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመም እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ የጉባዔው ተሳታፊ አባል አገራት ባላቸው የተለያየ ፍላጎትና አቋም ምክንያት ከስምምነት ሳይደረስ በቀጠሮ መተላለፉ ተገልጿል። በዘንድሮው ጉባዔ 200 ከሚሆኑ አገራት የተውጣጡ ከ29 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ማድሪድ ላይ ተሰባስበው ከህዳር 23 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም በየዘርፉ ሲመክሩ ሰንብተዋል። ከኢትዮጵያም ከአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከሲቪል ሶሳይቲ፣ ከክልል የአካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮዎችና ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ፈጻሚ አካላት የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። የዓመቱ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባዔ በይደር ያቆያቸው ወሳኝ ነጥቦች በመጪው ዓመት ጉባኤው በሚካሄድባት እንግሊዝ ከጥቅምት መጨረሻ እስከ ኅዳር 2013 ዓ.ም አጋማሽ በድጋሚ ይመከርባቸዋል።