የሲቪክ ማህበራት በተፈጠረላቸው የተመቸቻ የህግ ማዕቀፍ ፈጥነው ወደ ስራ አልገቡም - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪክ ማህበራት በተፈጠረላቸው የተመቸቻ የህግ ማዕቀፍ ፈጥነው ወደ ስራ አልገቡም
ኢዜአ ታህሳስ 9 / 2012 በኢትዮጵያ የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት በአሁኑ ወቅት የተፈጠረላቸውን የተመቻቸ የህግ ማዕቀፍ ተጠቅመው በተለይ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ግጭትና የሰላም እጦት ለመፍታት ፈጥነው ወደ ስራ አለመግባታቸው ተጠቆመ። የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማህበር ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ወንደሰን እንዳሉት የሲቪክ ማህበራት ባለፉት ዓመታት የመደራጀት መብታቸው ተነፍጎ በአገሪቱ የሰላምና ጸጥታ ግንባታ ተግባር እንዳይሳተፉ ተከልክለው ቆይተዋል።
ሆኖም የህግ ማእቀፍ ማሻሻልን ጨምሮ በአገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ የተወሰዱት የተለያዩ እርምጃዎች በአገር ሰላም ግንባታ ዙሪያ በትኩረት ለመስራት የሚያስችላቸው ድባብ የተመቻቸ ቢሆንም እየተጠቀሙበት አይደለም ብለዋል።
በተለይም በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም እጦት ችግሮችንና ግጭቶችን ለመከላከል ብሎም የግጭቱ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በማጥናትና አጥፊዎችንም በማጋለጥ ረገድ የሚገባቸውን ተግባር እያከናወኑ እንዳልሆነ ነው አቶ ንጉሴ የሚናገሩት።
የሲቪክ ማህበረሰብ ያገኙትን ምቹ ምህዳር በመጠቀም ፈጥነው ወደ ስራ መግባትና የተቋቋሙበትን ዓላማ በማሳካት አገሪቱንና ህዝቡን የማገልገል ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
የተለያዩ ሲቪክ ማህበራትን በቅንጅት አንቀሳቅሶ ለመስራት ያለው ክፍተት ለችግሩ አንዱ ምክንያት መሆኑም አቶ ንጉሴ ጠቅሰዋል።
የኖሬጂያን ቸርች ኤድ የሰላም ፕሮግራም ሃላፊ አቶ መንግስቱ ለገሰ በበኩላቸው ማህበራቱ በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችንና የሰላም እጦቶን ለመፍታት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በተለይ የሲቪክ ማህበራት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የመድረስ አቅም ስላላቸው ፈጥነው ችግሮችን የመፍታትና አጥፊዎችን የመለየት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ማህበራቱ የልማትና የሰብዓዊ እርዳታ ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ ባልተናነሰ ለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት ማህበራቱ ፈጥነው ወደሥራ በመግባት ለአገሪቱ ልማት፣ ሰላምና የህብረተሰብ ትስስር የማበልጸግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል።
በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶችን ሰላማዊና ዘላቂነት ባለው መንገድ የመፍታት ባህል እንዲዳብር ከሲቪክ ማህበራቱ ብዙ ይጠበቃል ሲሉም ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ በተለያየ ተግባር የተሰማሩ ሲቪክ ማህበራትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአገሪቱ ይንቀሳቀሳሉ።
ቀድሞ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1111/2011 በሚል ተሻሽሎ ጸድቋል።
የቀድሞ አዋጅ በርካታ ማነቆዎች የነበሩበት በመሆኑ ሲቪክ ማህበራትን ከሥራ ያስወጣ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ሊጫወቱ የሚገባቸውን ሚና ገድቦት እንደቆየ በዘርፉ የተሰማሩት ይገልፃሉ።