ቀጥታ፡

ለሠላም በጋራ ለመስራት መስማማታችን የቆየውን የመጠላለፍ ፖለቲካ ያስቀረዋል - ፓርቲዎች

ኢዜአ ታህሳስ  9/2012  የአማራና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ስለ ሠላም በጋራ ለመስራት መስማማታቸው ለዘመናት የዘለቀውን የመጠላለፍ ፖለቲካ የሚያስቀር በመሆኑ መደገፍ እንዳለበት  ተገለ ። ኢዜአ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክና ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አመራር አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል። የፓርቲዎቹ አመራሮች እንዳሉት የደረሱበት ስምምነት ከአሁን ቀደም የነበረውን የመጠላለፍ ፖለቲካ ወደ መነጋገርና በጋራ ወደ መስራት የሚቀይር በመሆኑ ሁሉም አካል ሊደግፈው የሚገባ ነው። ስምምነቱ ከአንድ ወር በላይ ማስቆጠሩንና ተቋማዊ አድርጎ ወደ ስራ ለመግባት ኮሚቴ ተዋቅሮ ቅድመ ሁኔታዎችና ደንቦች እየተዘጋጁ እንደሆነም ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ በተለያዩ መድረኮችና አደረጃጀቶች ላይ በሚገናኙበትና በተናጠልም በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በአገራዊ ሠላም ላይ አብረው መስራት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። ፓርቲዎቹ በአገራዊ ሠላም ላይ ትኩረት አድርገው መስራታቸው በህብረተሰቡ ዘንድ እምነት እንዲፈጠርና በምርጫውም ጥሩ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል። ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለዴሞክራሲና ለሠላም ያለውን አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ መሰረት አድርጎ እንዲንቀሳቀስ፤ ህዝቡም በዚሁ መሰረት መምረጥ እንዲችል የመገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና  ለሃምሳ ዓመታት ካለፍንበትን  የመጠላለፍ  ፖለቲካ፤  ወጥተን  ወደ  መደራደሩ፣ መነጋገሩ፣መግባባቱ  መምጣት አለብን ብዋል፡፡  የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አዲስ ሐረገወይን   በበኩላቸው   ቀጣዩ ምርጫና የዴሞክራሲ ግንባታ እውን እንዲሆን ከተፈለገ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ መንግስት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ሠላም ለማስፈን የገባውን ቃል መተግበር ይጠበቅበታል  ብለዋል፡፡ በአብን የእስካሁን እንቅስቃሴ በየክልሉ ያሉት አባላቱ ለሠላም እንዲሰሩና ከጥላቻ ነፃ ሆነው በአገራቸው ሠላም ላይ እንዲሰሩ ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሰጥተናል ሲሉም ተናግረዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም