የአገሪቷን የኃይል ችግር የሚያቃልሉ ሁለት የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የአገሪቷን የኃይል ችግር የሚያቃልሉ ሁለት የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ይፋ ሆነ
ኢዜአ ተህሳስ 9/2012 የመንግስትና የግል አጋርነት ትግበራ አካል የሆኑና የአገሪቷን የኃይል እጥረት ለመፍታት የሚያግዙ የሁለት የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ ዛሬ ይፋ ሆኗል። በሱማሌና በአፋር ክልሎች በ300 ሚሊዮን ዶላር የሚገነቡትን የጋድ እና ዲቼቶ የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አኳ ፓወር የተባለ የሳዑዲ ኩባንያ ይመራዋል። የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቶቹን ትግበራ ይፋ መሆን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ መቀመጫውን ሳዑዲ ዓረቢያ ያደረገው አኳ ፓወር ማሸነፉን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሾመ ታፈሰ ገልጸዋል። በመንግስትና በግል አጋርነት ፖሊሲ መሰረት ከኃይል ማመንጫ ጋር የተገናኙ 14 ፕሮጀክቶች የተለዩ ሲሆን ስምንቱ የፀሃይ፣ አምስቱ ደግሞ የውሃ ኃይል ማመንጫዎች ናቸው። ከስምንቱ የፀሃይ ኃይል ማመንጫዎች መካከልም የመጀመሪያዎቹና ሁለቱ የጋድ እና የዲቼቶ ፕሮጀክቶች በድምሩ 250 ሜጋዋት ኃይል ያመነጫሉ። ከፍተኛ የሆነውን የኃይል ፍላጎት በመንግስት በጀትና በብድር ብቻ መከወን ስለማይቻል ባለሃብቶች እየተወዳደሩ ወደ ዘርፉ እንዲገቡና ኃይል እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ዶክተር ተሾመ ተናግረዋል። በመጪዎቹ 10 ዓመታትም በመንግስት ሊተገበሩ ከሚችሉ ፕሮጀክቶች 50 በመቶውን የግሉ ዘርፍ እንዲሸፍንና አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፖሊሲ የተሳካ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ አንዷለም ሲያ በበኩላቸው መንግስት በኃይል አቅርቦትም ይሁን በሌሎች ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ቀዳሚ ሚና ነበረው ብለዋል። ያም ሆኖ የግሉም ዘርፍ ተሳትፎ በማስፈለጉ ይህ ፕሮጀክት መጀመሩን ገልጸው በተለይ የአገሪቷን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት እንደ አማራጭ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል። በሱማሌ ክልል የሚገነባው የጋድ ፕሮጀክት 18 ወራት፤ በአፋር ክልል የሚገነባው ዲቼቶ ደግሞ የ15 ወራት ጊዜ ይወስዳሉ ተብሏል። አኳ ፓወር የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚያመነጩትን ኃይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርብ ሲሆን ኩባንያው ስራውን ለ20 ዓመታት እንደሚያከናውን ተጠቁሟል።