ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ የ140 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

ታህሳስ 9/2012 በኢትዮጵያና በሳዑዲ ዓረቢያ ልማት ፈንድ መካከል የ140 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተፈረመ።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የተገኙ ሲሆን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የሳዑዲ የልማት ፈንድ ምክትል ሊቀመንበርና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ካሊድ ኤስ. አልኩዴሪ ስምምነቱን ፈርመዋል።

በብድር ከተገኘው ገንዘብ 75 ሚሊዮን ዶላሩ የደብረማርቆስ-ሞጣን የ118 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ለማገዝ ይውላል።

የዚህ መንገድ ግንባታ በአምስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተገለጸው 65 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ "ዋን ዋሽ" በሚል ለሚተገበረው መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ የሚውል ነው።

'ዋን ዋሽ' በገጠርና ከተሞች አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃና የአካባቢ ንፅህናን ለማጠናከር ታስቦ የተቀየሰ መርሃ ግብር ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2023 ይዘልቃል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የሁለቱ አገራት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይበልጥ እየተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሳዑዲ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የልማት ጉዞ በከፍተኛ የልማት ፋይናንስ እያገዘች መሆኗን ጠቁመው የዛሬው ስምምነት የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ ዜና የኃይል አቅርቦትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይቻል ዘንድ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ስምምነት ዛሬ ተፈርሟል።

'አኳ ፓወር' ከተሰኘው ኩባንያ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በተለይ በአፋርና ሱማሌ ክልሎች ከፀሃይ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት መሰረተ ልማት ግንባታ ይከናወናል፤ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ትብብርና ባለቤትነትም ይመራል።

ስምምነቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር  አብርሃም በላይ እና የአኳ ፓወር ኢንተርናሽናል ፕሬዚደንት ፓዳ ፓድማንተን ፈርመውታል።

የሳዑዲ የልማት ፈንድ ምክትል ሊቀመንበርና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ካሊድ አልኩዬሪ በበኩላቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

የአኳ ፓወር ኢንተርናሽናል ፕሬዚደንት ፓዳ ፓድማንተን ደግሞ ኢነርጂ ለኢኮኖሚ ልማት አስፈላጊ በመሆኑ በኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ በመሰማራታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር  አብይ አህመድ ከሳዑዲ የልማት ፈንድ  ምክትል ሊቀመንበርና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ካሊድ ኤስ. አልኩዴሪ እና ከልዑካን ቡድናቸው ጋር ኢንቨስትመንትና የልማት ድጋፍን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም