ፓርቲው ከከፋፋይ አሰራር የራቀ በመሆኑ ለአገሪቷ አንድነትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና ይጫወታል - የየካ ክፍለ ከተማ የፓርቲው አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው ከከፋፋይ አሰራር የራቀ በመሆኑ ለአገሪቷ አንድነትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና ይጫወታል - የየካ ክፍለ ከተማ የፓርቲው አመራሮች
ታህሳስ 9/2012 የብልጽግና ፓርቲ ከከፋፋይ አሰራር የራቀ በመሆኑ ለአገሪቷ አንድነትና ብልጽግና ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተገለጸ። የየካ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ በወረዳ ደረጃ በፓርቲው ሕግና ደንብ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ውይይት ማጠቃላያ ዛሬ አካሂዷል።
በክፍለ ከተማው የሚገኙ 14 ወረዳዎች በፓርቲው ሕግና ደንብ ላይ የተወያዩ ሲሆን ጥያቄዎችም ተነስተው ማብራሪያና ገለጻ ተደርጎባቸዋል።
ዛሬ በክፍለ ከተማው የሚገኙ የመሰረታዊ ድርጅቶችና ህዋስ አባላት በአዲስ አበባ ደረጃ ከተወከሉ አመራሮች ጋር በመሆን የፓርቲውን ውህደትንም አብስረዋል።
ወረዳዎችም ማጠቃላያ ሪፖርቱን ያቀረቡ ሲሆን በወረዳ ደረጃ የተነሱ ጥያቄዎች ላይም ማብራሪያ ቀርበዋል።
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም በፓርቲው ሕግና ደንብ ላይ የህወሃት ተወካዮች ለምን አልተገኙም? 'ፓርቲው ጨፍላቂ ነው' የሚሉና ከውክልና ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ናቸው።
ፓርቲው ከቀድሞ ኢህአዲግ ምን የተለየ ነገር ይዟል? አሁን ያለውን ችግር የሚፈታ ምን የተለየ ነገር ይዟል? የመሳሰሉትም ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ይገኙበታል።
የየካ ክፍለ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ በመደመር ጽንሰ ሀሳብ በወቅታዊው ሁኔታ ያሉ ግርታዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
''መደመር ትናንትን በመውቀስ ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም'' ያሉት ኃላፊው፤ መልካም አገራዊ እሴቶችን በመሰብሰብ፤ ካለፈው በጎ ነገሮችን መውሰድና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር መፍጠርን ዓላማ ያነገበ እንደሆነ ተናግረዋል።
አገራዊ አንድነትን ማረጋገጥ የፓርቲው ዋና አላማ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ፓርቲው ከፋፋይ ከሆኑ አካሄዶች የራቀ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ይላሉ።
''ድርጅቱ ከዚህ በፊት የሚመራበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የከፋፋይነት ዝንባሌ ያለው ነበር'' ያሉት አቶ ዘመኑ፤ "ትምክህትና ጠባብ፣ ልማታዊ ባለኃብትና ኪራይ ሰብሳቢ ባለኃብት፣ ምሁርና ወላዋይ የሚሉ አገላለጾች" በስፋት ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር ሲሉም ተደምጠዋል።
አቶ ዘመኑ አክለውም "አብዮታዊ ዲሞክራሲ መልካም ነገሮች ቢኖሩትም በተለይ የአፋኝነት ባህሪ የነበረው በመሆኑ ዲሞክራሲው ወደ ፊት እንዳይጓዝ አድርጓልም" ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ግን "ዴሞክራሲ በስምምነት ላይ መመስረት አለበት" የሚል አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የፓርቲው ማህበራዊ መሰረትም የኢትዮጵያ ዜጎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
አገሪቷ የገባችበት ቀውስ ውህደቱን አስፈላጊ እንዳደረገው የገለጹት ኃላፊው፤ ''ልንጠፋፋ ተቃርበን ነበር፤ አገርን ከማስቀጠል አንጻር የፓርቲው መምጣት ተገቢ ነው" የሚል ሀሳብም ሰንዝረዋል።
የፓርቲው እውን መሆን ከሕገ መንግሥቱና ፌዴራል ሥርዓቱ ጋር አይገናኝም ብለዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ለገሰ በበኩላቸው "ፓርቲው የመጨፍለቅ እሳቤ አለው እየተበለ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ስለ ፓርቲው ትክክለኛ ግንዛቤ ካለመያዝ የመነጨ" እንደሆነ ተናግረዋል።
የፓርቲው የሥራ ቋንቋ አምስት እንዲሆን መወሰኑ አሳታፊ እንደሆነ አመላካች እንደሆነ ጠቅሰው፤ ''ኢትዮጵያ የተሳፈረችበት መርከብ ሁሉንም የሚያቅፍ ነው'' በማለት ነው ፓርቲው ጨፍላቂ አለመሆኑን ያስረዱት።