በኢትዮጵያና ሳኡዲ አረቢያ ልማት ፈንድ መካከል የ140 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ሳኡዲ አረቢያ ልማት ፈንድ መካከል የ140 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈረመ
ኢዜአ ታህሳስ 9/2012.. በኢትዮጵያና ሳኡዲ አረቢያ ልማት ፈንድ መካከል የ140 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተፈረመ። በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት በተከናወነው የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ተገኝተዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የሳኡዲ የልማት ፈንድ ምክትል ሊቀመንበርና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ኻሊድ አልኩዬሪ የብድር ስምምነቱን ፈርመዋል። በብድር ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ 75 ሚሊዮን ዶላሩ ከደብረማርቆስ አስከ ሞጣ ያለውን 118.4 ኪሎ ሜትር መንገድ ፕሮጀክት ለማገዝ ይውላል። የመንገድ ግንባታው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተመለከተው ከገንዘቡ መካከል 65 ሚሊዮን ዶላሩ "ዋን ወሽ" በሚል ለሚተገበረው መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ የሚውል ነው። 'ዋን ወሽ' በገጠርና ከተሞች አካባቢ ንጹህ የመጠጥ ውሃንና አካባቢ ንፅህናን ለማጠናከር ታስቦ የተቀየሰ መርሃ ግብር ሲሆን እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ 2023 የሚቆይ ነው ተብሏል። በሌላ ዜና የኃይል አቅርቦትን ለማጠናከር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይቻል ዘንድ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ስምምነትም በዛሬው እለት ተፈርሟል። 'አኳ ፓወር' ከተሰኘው ኩባንያ ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በተለይ በአፋርና ሱማሌ ክልሎች በፀኃይ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት መሰረተ ልማት ግንባታ ይከናወናል፤ ፕሮጀክቱም በመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብርና ባለቤትነት ይመራል።