ቀጥታ፡

2ተኛው የኢትዮ-ሳውዲ አረቢያ ቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄደ

ኢዜአ ታህሳስ 8/2012 ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ ኩባንያዎች ያገናኘ የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። የኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ ኩባንያዎችን ፊት ለፊት ያገናኘው የቢዝነስ ፎረም ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል ተካሂዶ የነበረ ሲሆን በፎረሙ ከ150 በላይ ባለሃብቶች መሳተፋቸው የሚታወስ ነው። የዚሁ የቢዝነስ ፎረም አካል የሆነ ሁለተኛው ኢትዮ-ሳውዲ አረቢያ ቢዝነስ ፎረም ዛሬ ተካሂዷል። ፎረሙ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የሳዑዲ የወጪ ንግድ ልማት ባለስልጣን የንግድ ልኡክ መርሃ ግብር አማካኝነት ነው። በመድረኩ ከ40 በላይ የሳውዲ ባለኃብቶች እና 30 ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል የተለያዩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ፎረሙ የአገራቱን ጠንካራ ፖለቲካዊ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሳኡዲ አረቢያ እንደመኖራቸው መጠን የቢዝነስ ፎረሞችን ማጠናከር ለሁለቱም አገራት ኢኮኖሚ መጠናከር አስተዋፆ ያበረክታል ብለዋል። ኢትዮጵያ ወደሳኡዲ ከምትልካቸው ምርቶች ቡናና ስጋ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ይጠቀሳሉ ያሉት አምባሳደር ደዋኖ ይሁን እንጂ ሳውዲ ለኢትዮጵያ ካላት ቅርበት አንፃር ከአገሪቱ ጋር ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ብዙ አልተሰራም ሲሉ ተናግረዋል። ለአብነትም ከአውሮፓ፣ አሜሪካ እና እስያ አገራት ገበያ አንፃር ሳውዲ ትልቅ የገበያ እድል ያላት እና የእርሻ ምርቶች በስፋት የሚፈለግባት አገር እንደመሆንዋ መጠን በዚህ ዘርፍ የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶችን በመላክ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል አብራርተዋል። ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ምርት መጠን 187 ሚሊዮን ዶለር የደረሰ ሲሆን ከኢትዮጵያ ወደ ሳውዲ የሚላከው ምርት ግን 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህ የንግድ ልውውጥ ሚዛን ልዩነትን ለማመጣጠን ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ልማት ላይ ከፍተኛ ስራ መስራት እንደሚገባት አምባሳደሩ አስምረውበታል። የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ሚዛናዊ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ ወደሳውዲ ከምትልካቸው ምርቶች የምታስገባቸው ምርቶች መብዛታቸው መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በግብርና ውጤቶች፣ በመድሃኒት፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና በሌሎች ዘርፎችም ትልቅ አቅም ያላት ቢሆንም በወጪ ንግድ ዘርፍ የሚደረገው ማበረታቻ እምብዛም ባለመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርቶችን ወደውጪ ከመላክ ይልቅ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትን እንደአማራጭ ይከተላሉ ብለዋል። ይህ ደግሞ ተጠቃሚው ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ አሁን ላይ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የተለዩ ማበረታታዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ወደፊት በወጪ ንግድ ዘርፍ መሻሻል ይኖራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አብራርተዋል። በኢትዮጵያ የሳኡዲ አምባሳደር ሳሚ ጃሚል አብደላ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ሳውዲ አረቢያ ከምን ጊዜውም በተሻለ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። ለረዥም ጊዜ በቆየው የአገራቱ ሁለትዮሽ ግንኙነት ምክንያት የንግድና ቢዝነስ ግንኙነቱ እለት ተዕለት እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል። እያደገ የመጣውን የቢዝነስ ግንኙነት ወደፊት ለማራመድ ኢትዮጵያ ለንግድ ደህንነት ማረጋገጫ ሊሰጥ በሚችል መልኩ አሰራሮችን ማሻሻል ይገባታል ብለዋል። በሁለቱ አገራት መካከል በአውሮፓ አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2018 ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድረሱ ይገመታል። ይሁን እንጂ በሁለቱ አገራት ባለው የንግድ ልውውጥ አብዛኛውን ተጠቃሚነት ወደሳውዲ ያደላ ነው። በተመሳሳይ ዓመት ሳውዲ ወደአገሯ ካስገባችው የኢትዮጵያ ምርቶች ወደኢትዮጵያ የላከችው በ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብልጫ አለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም