አገራዊ የአንድነት ለውጡን ለማስቀጠል ተግተን እንሰራለን-የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ የአንድነት ለውጡን ለማስቀጠል ተግተን እንሰራለን-የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2010 አሁን እየተፈጠረ ያለውን ሀገራዊና ኢትዮጵያዊ አንድነት ለውጡን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ። የኃይማኖት ተቋማቱ ከአሁን ቀደምም በሰላምና በፍቅር ላይ እየሰሩ የቆዩ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን የተፈጠረው ለውጥ ግን እስካሁን ሲሰሩት ለነበረው የሰላምና የፍቅር ስራቸው የበለጠ ምቹ ሁኔታን የፈጠረላቸው መሆኑን ይገልጻሉ። የኃይማኖት አባቶቹ በድጋፍና እውቅና ሰልፉ ላይ ተገኝተው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ሰልፉ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተካተቱበትና ኢትዮጵያዊነትን የበለጠ የሚያንጸባርቅ መሆኑንም ተናግረዋል። መጋቢ ኃይማኖት ስምዖን፣ ሼክ ያሲን አህመድ እንዲሁም አቶ ቁፋ ጎቤ የሀገር ሽማግሌዎች እንደተናገሩት አሁን በአገሪቷ እየተፈጠረ ያለው አገራዊና ኢትዮጵያዊ ለውጥ መገለጫ በሆነው ሰልፍ ላይ ተገኝተው የቆየውን ኢትዮጵያዊ አንድነትና ፍቅር እንደሚሰብኩም አረጋግጠዋል። የኃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ እንዳሳሰቡት ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅና እየተፈጠረ ያለው ለውጥ ቀጣይ እንዲሆን ሁሉም በየፊናው ተግቶ መስራት አለበት።