ቀጥታ፡

ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ይጀመራል

ኢዜአ ታህሳስ 8/2012 የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ በሆሳዕና ይጀመራል። ውድድሩ ዛሬ ሲጀመር ከ91 ኪሎ ግራም በላይ ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከስምንት ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ጎንደር ከተማ፣ ሀድያ ዞን፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና የሶማሌ ከተማ የቦከስ ክለቦች የውድድሩ ተሳታፊ ናቸው። በወንዶች ከ52 እስከ ከ91 ኪሎ ግራም በላይ፤ በሴቶች ከ51 እስከ 60 ኪሎ ግራም ውድድሩ የሚካሄድባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የውድድሩ አላማ በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር በቦክስ ስፖርት ለመሳተፍ የካቲት 2012 ዓ.ም በሴኔጋል ለሚካሄደው የማጣሪያ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች መምረጥ ነው። ውድድሩን በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ ለቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጭን እንደሚያሰፋ ተናግረዋል። ዛሬ ከሰአት ውድድሩ ሲጀመር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ከ91 ኪሎ ግራም በላይ ወንዶች የድሬዳዋ ከተማው ሊበን አህመድ ከፌዴራል ፖሊሱ ባህሩ ሽፈራው ጋር የፍጻሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በዛሬው መርሃ ግብር ከ91 ኪሎ ግራም በላይ ወንዶች የፍጻሜ ውድድር በተጨማሪ በ57 ኪሎ ግራም ወንዶች እና በ51 ኪሎ ግራም ሴቶች የማጣሪያ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ዓመቱ ውስጥ የሚካሄዱ ቀሪ ሶስት ውድድሮች በጎንደር፣ በወላይታ ሶዶና አዲስ አበባ ከተሞች እንደሚካሄዱ አቶ ስንታየሁ ጠቁመዋል። በአራቱ ከተሞች የሚካሄዱት ውድድሮች አጠቃላይ ውጤት ተደምሮ በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ክለቦች እንደሚለዩም አስረድተዋል። የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ይቆያል። ፌደራል ፖሊስ በወንዶች አዲስ አበባ ፖሊስ በሴቶች የ2011 ዓ.ም ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም