ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጡ ለኑሮና ለስራ ጫና ዳርጎናል----በአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችና የፋብሪካ ተወካዮች

ኢዜአ ታህሳስ 8  2012 ---በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ያለው ውስብስብ ችግር በኑሮና በስራቸው ላይ ጫና መፍጠሩን የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችና የፋብሪካ ተወካዮች ገለፁ። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ከደንበኞች ጋር ትናንት በአሶሳ ከተማ ተወያይቷል፡፡ የከተማው ነዋሪ አቶ አከለ አጥናፉ በሰጡት አስተያየት በከተማው መብራት በየቀኑ እንዲሁም በየሰዓቱ ስለሚቋረጥ በኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ላይ ተደጋጋሚ ብልሽት አድርሶባቸዋል። "የሚበላሹ እቃዎችን ለመተካትና ለማስጠገን ለአላስፈላጊ የገንዘብ ወጭ ተዳርጊያለሁ" ብለዋል። አቶ ጌታቸው ሰጠኝ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ተቋሙ የጀመረው አዲስ የክፍያ መቀበያ ስርዓት አገልግሎቱን ከማቀላጠፍ ይልቅ ያወሳሰበው መሆኑን ጠቁመዋል። አሰራሩ ከተጀመረ ወዲህ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ለረጅም ወራት ቢል ሳይመጣላቸው በመቆየቱ ለውዝፍ እዳ መዳረጋቸውን ተናግረዋል። “ለአገልግሎት ክፍያ ብመላለስም ቢል የለም በሚል የተጠቀምንበት የ500 ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እዳ አለብኝ” ያሉት ደግሞ አቶ መረሳ ገብረሥላሴ ናቸው ። አንዳንድ የቆጣሪ አንባቢዎችም የስነ- ምግባር ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ውስብስብነት ነዋሪውን ለኑሮ ጫና የዳረገው በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው አመላክተዋል። ከከተማው "ዚጊ ዱቄት ፋብሪካ" የተወከሉት አቶ ብዙ አባይ በበኩላቸው ፋብሪካው በቀን 820 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ቢኖረውም በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ከአቅም በታች ለአራት ሰዓት ብቻ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአሶሳ ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን የዘይት ፋብሪካ ተወካይ አቶ አባተ ጸጋዬ በበኩላቸው ለፋብሪካው ኃይል የሚያስተላልፍ ትራንስፎርመር ላጋጠመው ብልሽት ተገቢው ጥገና ባለመደረጉ ከ47 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማስወጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ "በተቋሙ እየተስተዋለ ያለው የኃይል አቅርቦት ማነስና የአገልግሎት አሰጣጥ መንዛዛት በፋብሪካዎቹ ሥራ ላይ ስጋት የፈጠረ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል "ሲሉ ተወካዮቹ ጠይቀዋል ። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኤሌክክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ከበደ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች መላሽ ሰጥተዋል ። በከተማው ያለአግባብ የተተከሉ የማንጎና የባህር ዛፍ ተክሎች ከኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር በመነካካታቸው ለኃይል መቋረጥ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል ። “ቆጣሪ አንባቢዎቻች የክህሎትና የሥነ-ምግባር ችግር እንዳለባቸው ደርሰንበታል” ያሉት ስራ አስፈጻሚው ችግሩን በአጭር ጊዜ ፈትሾ ለማረም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ። ደረጃውን ባልጠበቀ ጥገና የሚያጋጥም የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት የባለሙያ አቅም የመገንባትና የደንበኞች ግንኙነት ስራዎች እንደሚከናወኑም አመላክተዋል ። ተቋሙ ኢንሹራንስ እንዳለው የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚው፣ ደንበኞች በኤሊክትሮኒክስ እቃዎቻቸው ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በወቅቱ አሳውቀው ጉዳዩ ተጣርቶ ሲረጋገጥ ካሳ የሚከፈልበት አሰራር መኖሩን አስታውቀዋል ። ከፋብሪካዎች በኩል የኃይል እጥረት ስለመኖሩ ለተነሳው ቅሬታ ተአማኒነት እንደሌለው በመግለፅ ከደንበኞች ጋር ተቀራርቦ በመነጋር የሚፈቱ ችግሮች መሆናቸውን አመላክተዋል። የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋዝ "ቢሮው ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በክልሉ የኃይል ቅርቦት እንዲጠናከር ይሠራል" ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም