ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ና ደላሎች ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል

146

ኢዜአ፤ታህሳስ 8/2012 'ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ደላሎች ህገወጥ ስደትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎታል' ሲል በኢትዮጵያ የአለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አስታወቀ። የስደት ችግር እየተስፋፋ መምጣቱም ተነግሯል።

አይኦኤም አለም ዓቀፍ የስደተኞች ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ ህገ ወጥ ስደትን በመከላከል ረገድ በርካታ ስራዎችን ብትሰራም እየተስፋፋ ከመጣው የስደት ችግር አንጻር ቀሪ ተግባራት አሉ።

በኢትዮጵያ የአይኦኤም ተልዕኮ አስፈጻሚ ማውሪን አቺንግ በመግለጫው ላይ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ላለፉት አመታት በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት በስራ ፈጠራ ለዜጎች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ትልቅ ስራ ሰርታለች።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ መካከለኛው ምስራቅ በህገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ችግር ለመቀነስ ከአገሮቹ ጋር ህጋዊ የስራ ስምምነቶችን ማድረጓ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ተገልጿል።

በጎረቤት አገሮች የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ይኖሩ የነበሩና ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎችን በመመለስ ረገድም ትልቅ ስራ መሰራቱን ሃላፊዋ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችና ደላሎች በየቀኑ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታ  ዜጎች እየተሰደዱ

መሆኑን ተናግረው፤ ችግሩን ለማቃለል ከኢትዮጵያ የሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ለህገ ወጥ ስደት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ለይተን እየሰራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ህገ ወጥ ስደትን ለማስቀረት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪም በስደት ለሚኖሩ ሰዎች በቂ የማህበራዊ አገልግሎትና የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ  መንግስታትና አጋር ደርጅቶች ትኩረት አድርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ መንግስት በህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም