ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ክፉ ነገር ይርቃት ዘንድ ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ሊረባረብ ይገባል

ኢዜአ፤ታህሳስ 8/2012 በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያን ያንዣበባት ክፉ ነገር ርቋት በጎ ሁኔታዎች ይገጥሟት ዘንድ ሕዝቡ ምን ማድረግ ይኖርበት ይሆን?

'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' የተሰኘው ድርጅት በቅርቡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ አጠቃላይ ሁኔታ ይመለከታቸዋል ያላቸውን 50 ሰዎች አሰባስቦ ሲያወያይ ቆይቷል።

50ዎቹ ሰዎች ውይይታቸውን ሲያገባድዱም ኢትዮጵያ በ2032 ዓ.ም ሶስት ክፉ ነገሮችና አንድ በጎ ነገር ሊገጥማት ይችላል ደግሞ በውይይቱ የተደረሰባቸው ትንቢቶች ናቸው።

ይህ 'አራቱ ሴናሪዮ' በመባል የተቀመጠው ያለፈውን የገመገመ፣ አሁን ያለውን ሁኔታ ተንትኖ መጪውን በተነበየው ሂደት ክፉ ነገሮች በርከት ያሉበት ነው።

የሴናሪዮ ቡድን አባል በመሆን መጪውን ጊዜ የተነበዩት ሰዎችም ፍጹም የተራራቀ ሃሳብና ግብ የነበራቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ነበሩ።

ለመሆኑ ስጋቱ ምን ያህል አሳሳቢ ቢሆን ነው እነዚህ 'ሻይ ቡና' እንኳን በጋራ መጠጣት የማይችሉ የተለያየ ዓለም ሰዎች በአንድ ድምጽ የተስማሙት?

የ'ዴስቲኒ ኢትዮጵያ' ኃላፊ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክፉ ሁኔታዎች እጅግ ያሳስባሉ ካሉ በኋላ እነሱንም ለማራቅ በጋራ መስራት ብርቱው አማራጭ መሆኑን ይናገራሉ።

ከሴናሪዮዎቹ መካከል አደጋ ያዘሉት በ'ሰባራ ወንበር'፣ 'አጼ በጉልበቱ'ና 'የፉክክር ቤት' በመባል ተገልጸዋል ይላሉ አቶ ንጉሱ።

ሴናሪዮዎቹ የሚያመለክቱትም በከፍተኛ ደረጃ ቍጥሩ እያደገ ለሚሄደው ሕዝብ ፍላጎቱን ማሟላት አለመቻል በመንግስት ላይ ጫና እየፈጠረ በመሄድ ትልቅ አደጋ መደቀኑን ነው።

ይህን አስታኮም ፈላጭ ቆራጭነት ይነግስና ሕዝቡ በተነቃቃ መንፈስ አገሩን ማሳደግ ትቶ መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ይገባል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

አደጋው ከዚህም ከፍቶ የተለያዩ ቡድኖች እንደፈለጉትና እንደመሰላቸው ስለሚወስኑ በሂደቱ የፌዴራል መንግስት ሊፈረካከስ ይችላልም የሚል ሰጋት መኖሩንም አልሸሸጉም።

የሴናሪዮ ቡድን አባላቱን ለከፍተኛ ስጋት ውስጥ የከቱት እነዚህ አገራዊ አደጋዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል።

በተለይም ከ50ዎቹ መካከል 25 ገደማ የሚሆኑት የፖለቲካ ድርጅት ተወካዮች ሲሆኑ እነሱም ሃሳቡን ለአገር ጠቃሚ በሆነ መልኩ ሊተገብሩት ዝግጁነታቸውን አሳይተዋል።

አቶ ንጉሱ ዋናው ጉዳይ በ'ንጋት' የተመሰለው ሴናሪዮ ዕውን እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአደጋውን ልክ ተረድቶ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ከነዚህ መካከል ዋናው መደረግ ያለበት ጉዳይ እርቅና ይቅርታን የእለት ተእለት ተግባር በማድረግ አሁን የሚታዩትን ቅራኔዎች መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ህዝቦችን እያራራቁ ከሚገኘው ችግሮች መካከል የታሪክ ትርክቶችን መነሻ በማድረግ የሚፈጠሩ ንትርኮች እያሳደሩ ያሉትን አሉታዊ ተጽዕኖዎችን መቀነስ እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ አቶ ንጉሱ።

''ከምንም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት ጉልበተኝነትንና ጩሀትን ቀንሶ መደማመጥና መነጋገር፣ ብሎም መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ሌላው አስፈላጊና መደረግ ያለበት ያሉት ደግሞ በተለይም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመጥቀስ  የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ነው።

የዴሞክራሲ ተቋማት ሲጠናከሩ በሕዝብና በሕዝብ እንዲሁም በሕዝብና በመንግስት መካከል ከፍተኛ መተማመን ይፈጥራሉ በማለት።

የሴናሪዮ ዝግጅት ቡድኑ ውስጥ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እንዲሁም የማህበረሰብ አንቂዎች ተሳትፈውበታል።

'ዴስቲኒ አትዮጵያ' በአገሪቷ እየታየ ላለው የፖለቲካ አጣብቂኝ አማራጭ የመፍትሔ ሃሳብ ለማቅረብ የተደራጀ ሲሆን መሰል ተቋማት በ20 አገራት እየተንሳቀሱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም