ውጤታማ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር ምቹ ፖሊሲና የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ይገባል

89

ኢዜአ፤ ታህሳስ 7/2012 በኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው ጠንካራ የምጣኔ ኃብት እድገት ለማስመዝገብ ከአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር በተያያዘ የሚያሰሩ ፖሊሲዎችን መቅረፅና ምቹ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተገለፀ።

ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማምጣትና ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ።

ሆኖም በኢትዮጵያ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማትን ለማስፋፋት የሚደረገው ጥረት ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም የሚፈለገው ለውጥ እንዳልመጣ ይነገራል።

ለዚህም ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል ዘላቂ የሆነ የብድር አቅርቦት እጥረትና ምቹ የአሰራር ስርዓት አለመኖር በዋናነት ይጠቀሳሉ።

የፌዴራል አነስተኛና መካካለኛ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎች በዘርፉ መልካም ተመክሮ ባላት ቪየትናም በቅርቡ ጉብኝት አድርገዋል።

ከጉብኝቱ የተገኘውን ልምድ ከክልልና ከማዕከል ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ለማጋራት በተሰናዳው መድረክ ላይ እንደተገለፀው ቪየትናም ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት የነበራት የምጣኔ ኃብት ሁኔታ እና አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን አገሪቱ ጠንካራ የምጣኔ ኃብት መገንባት ችላለች።

ይህ የምጣኔ ኃብት እድገት እውን እንዲሆን ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት ደግሞ  የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መሆናቸውን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ይናገራሉ።

አገሪቱ ላለፉት 30 ዓመታት የተገበረችው የምጣኔ ኃብት ልማት እቅድ የአነስተኛና መካካለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማእከል ያደረገ በመሆኑ እድገቷን ለማፋጠን እንደቻለች ነው አቶ አስፋው የሚገልፁት።

ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጉ ፖሊሲዎችና መመሪያዎችን በመቅረጽና በመተግበር እንደዚሁም  እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በማስቀረት ዘርፉን ማልማት እንደሚቻልም ነው ከቪየትናም መማር የሚቻለው ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም በቂ የብድር አቅርቦት፣ ዘርፉ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል በትምህርትና በስልጠና ማበልጸግና ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት የግድ መሆኑንም ከጉብኝቱ መገንዘባቸውን ገልፀዋል።

የቪየትናም መንግስት ለሴቶች አደረጃጀትና በዘርፉ ለሚሰማሩ የግል ባንኮች የተለያዩ የድጋፍና ማበረታቻ ማእቀፎችን በማዘጋጀት አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት የተደረገው እንቅስቃሴ ለውጤቱ ቁልፍ ሚና መዋወቱንም አንስተዋል።

 በዚህም በአገሪቱ ከተፈጠረው የስራ እድል 50 በመቶ የሚሆነውን ያስገኙት በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩት አካላት ናቸው ብለዋል።

የመንገድ ላይና የትላልቅ ሆቴሎች ንግድ በአግባቡ ተመርቶ ለስራ እድል ፈጠራና ለዜጎች ሃብት ማፍሪያ እንዲሆን መደረጉም እንዲሁ።

ቪየትናም ባለፉት ሶስት አስር አመታት ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በሰጠችው ትኩረት ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ ከፍተኛ ባለሃብቶችን መፍጠር መቻሏንም አክለዋል።

የቪየትናም ህዝብ የአገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህሉም የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉና ምርታቸውን በብዛት አንዲያመርቱ  እድል ፈጥሯል።

በፌዴራል የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ እሸቱ ሁሴን እንደሚሉት የመንገድ ዳር ነጋዴዎችን ጨምሮ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ምርትና ግብይት ለተሰማሩ አካላት የሚሰጠው ትኩረት፣ ምቹ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠር የሚደረገው ድጋፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተመክሮ ነው ይላሉ።

ቪየትናም የጥቃቅንና አንስተኛ በአብዛኛው የተሰማሩት በግብርና ማቀነባባርና በማኑፋክቸሪንግ ላይ በመሰማራታቸው ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር ችለዋል ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ጥላሁን ታደሰ በአዲስ አበባ ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው በቪየትናም የተቀናጀ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት አሰራርና ውጤትን አይተናል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም