የኦሮሞ አባገዳዎች ሀገራዊ ትስስርን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

88
ኢዜአ፤ ታህሳስ 7/2012 የኦሮሞ አባገዳዎች የካበተ የግጭት አፈታት ባህላዊ ልምዳቸውን በመጠቀም ሀገራዊ ትስስርን ለማጠናከር የድርሻቸውን አንዲወጡ የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጠየቁ። በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አባገዳዎች የተሳተፉበት የእርቀ ሰላም የውይይት መድረክ ዛሬ በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ ተካሂዷል። በዚህ ወቅት  የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ተቀዳሚ ሙፊቲ ሀጂ ኡመር እንዲሪስ እንዳሉት አባገዳዎች ጥልቅ የሆነ የችግር አፈታት ባህል ባለቤቶች ናቸው። "ይህን ባህል ለሠላም፣ለአንድነት፣ለሀገርና ህዝብ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው "ያሉት ሀጂ ኡመር ይህንን እሴት አባገዳዎች በማጎልበት ሀገራዊ ትስስርን ለማሳደግ ከኮሚሽኑ ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጠይቀዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሀገሪቱ ችግር ገጥሟት እንደነበር   አስታውሰው "ከዚህ ችግር በዘላቂነት ለመላቀቅ አባገዳዎች ያላቸውን ተሳትፎና ወሳኝ ሚና ማጠናከር" ያስፈልጋል ብለዋል። ሌላው የኮሚሽኑ አባል ዶክተር አበራ ዴሬሳ በበኩላቸው በሀገሪቱ የነበሩ አለመግባባቶች  ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈቱ ለማድረግ ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ በእውነትና ሀቅ ላይ የተመሰረተ ትንተና ለማድረግ፣ የችግሩ ባለቤትና ያስከተለው ጉዳት ተለይቶ ጉዳት አድራሹ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ተበዳዩም ይቅርታውን እንዲቀበል ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። እርቅ ለማምጣት የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመለየት ጀምሮ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት በየደረጃው የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። "በዚህ ረገድ ኦሮሚያ ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱትና ማንኛውንም ችግሮች ሲፈቱ የነበሩት አባገዳዎች ናቸው" ያሉት ዶክተር አበራ በኮሚሽኑ ሥራ ሂደት ውስጥ የአባገዳ ሚናን ልምድ ለመውሰድ፣ የመንግስትን አቅጣጫ ለማስታወቅና በጋራ ለመምከር በማሰብ መድረኩ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል። የኦሮሞ አባገዳዎች የካበተ የግጭት አፈታት ባህላዊ ልምዳቸውን በመጠቀም ሀገራዊ ትስስርን ለማጠናከር የድርሻቸውን እንዲወጡ የኮሚሽኑ ጠይቀዋል። አባገዳዎች በተለይ ኢንዱስትሪዎች አካባቢ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን በግንባር ቀደምትነት ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሲፈቱ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ኦሬሳ ናቸው። አባገዳዎች ያላቸውን ልምድ በመጠቀም እንዴት ኮሚሽኑን እንደሚያግዙ በማሰብ መድረኩ መዘጋጀቱ አባገዳዎችን ይበልጥ  የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም