በደቡብ ክልል የደረሰ ሰብልን ፈጥኖ ለመሰብሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል የደረሰ ሰብልን ፈጥኖ ለመሰብሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ኢዜአ ታህሳስ 7/2012 በደቡብ ክልል በ2011/2012 የምርት ዘመን አርሶ አደሩ ያለማውን የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ አንድ ሚሊዮን 11 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፍኗል። ከዚህም ውስጥ 56 በመቶ የሚሆነው መሰብሰቡን አመልክተዋል። በዋናነት ምርት ሲሰበሰብ ቆየው በማዕከላዊ የክልሉ ዞኖች እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳንኤል "ከነዚህ ዞኖች ከ90 በመቶ በላይ ምርት ተሰብስቧል "ብለዋል ፡፡ የተቀረው ደግሞ በአብዛኛው ደጋማ የክልሉ አካባቢዎች ላይ የሚገኝ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ እንደ ቢሮው ምክትል ኃላፊ ገለጻ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አሁንም የሚቀጥልበት ሁኔታ እንዳለ የአየር ሁኔታ ቅድመ ትንበያ መረጃ ያመለክታል። 44 በመቶ የሚሆነው ቀሪው ሰብል እየደረሰ ያለ በመሆኑ ለጉዳት ሳይጋለጥ ከስር ከስር መሰብሰብ የሚገባው እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡ ቀደም ሲል ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ የተዋቀረውን የምርት አሰባሰብ ግብረ-ኃይል በማንቀሳቀስና ህብረተሰቡን በማስተባበር ቀሪውን ምርት ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ ነው። በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ አካላት፣፣ ተማሪዎችን፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር በተለይ የአቅመ ደካሞችና ሰፋፊ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች ምርት ከወዲሁ ፈጥኖ ለመሰብሰብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ከፍላጎቱ ብዛት አንጻር ተመጣጣኝ ባይሆንም ኮምባይነሮች ወደ ክልሉ መግባታቸውን ያመለከቱት አቶ ዳንኤል ገልፀው አርሶ አደሮችን አደራጅቶ ከኮምባይነር ባለቤቶችና ማህበራት ጋር በማገናኘት የደረሰ ሰብልን በፍጥነት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በክልሉ በምርት ዘመኑ ከለማው መሬት 98 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ፡፡