አሰሪና ሠራተኛው በጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የእርስ በርስ ውይይት ሊዳብር ይገባል--የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አሰሪና ሠራተኛው በጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የእርስ በርስ ውይይት ሊዳብር ይገባል--የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
ኢዜአ፤ ታህሳስ 7/2012 አሰሪውና ሠራተኛው ሚዛናዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የእርስ በርስ ግንኙነታቸው በውይይት ሊዳብር እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአማራ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያዘጋጀው የመንግስት፣ የአሰሪ እና ሠራተኛ የሦስትዮሽ የምክክር ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ የተገኙት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መጥቷል።
እንደ አገር የሠራተኛውንም ሆነ የአሰሪውን ጥቅም ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ቢሆንም የሠራተኛውን መብት ከመጠበቅ አኳያ አሁንም ሰፊ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በሕገ የተፈቀዱ የሰራተኛውን የመደራጀት መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚገደብበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመፍታት የአሰሪና ሠራተኛ ተወካዮች እርስ በርስ ተደጋግፈው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
"ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የአሰሪውም ሆነ የሠራተኛው መብት እንዲጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።
በአገርም ሆነ በክልል ደረጃ በመንግስት፣ በአሰሪ እና በሠራተኛው ላይ ከፍተት መኖሩን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ናቸው።
እንደኃላፊዋ ገለጻ መንግስት አሰሪውም ሆነ ሠራተኛው የሚያነሰውን ጥያቄ በአግባቡ አዳምጦ ለመፍታት የመዋቅርም ሆነ የሰው ኃይል መጠንና የአቅም ውስንነት አለበት።
በሠራተኛውና በአሰሪው መካከል የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት ከፌዴራል አስከ ክልል ለዘርፉ ሰፊ ትኩረት መስጠትና እስከወረዳ ድረስ መዋቅር ዘርግቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተመሳሳይ አሰሪው አካል ለራሱ ጥቅም ብቻ በመቆም የሠራተኛውን ተደራጅቶ መብትን ከመጠየቅ ጀምሮ ሲቃወም እንደሚስተዋል ነው የገለጹት።
ሠራተኛውም ተቀጥሮ ለሚሰራበት ኢንዱስትሪ ትርፋማነት ሳይሆን ከራሱ ጥቅም አንጻር ብቻ በማየት ጥያቄዎችን እንደሚያነሳ ዶክተር ሙሉነሽ አመልክተዋል።
"ይህንን ችግር ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እርስ በርስ በመገናኘትና በመወያየት ችግሮችን መፍታትና ለጋራ ተጠቃሚነት መትጋት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

የምክክር ጉባዌው ዓላማም ይሄ መሆኑን ነው ኃላፊዋ የገለጹት።
"ትርፋማ ሆኖ ራስንም ሆነ አገርን ለመጥቀም የሠራተኛውን መብት መጠበቅ ይገባል" ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል ናቸው።
ለእዚህም አሰሪ አካል ሙያው በሚጠይቅው እውቀት ላይ ሠራተኛውን በማስልጠን ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ነው የገለጹት።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ባለሃብቶችም ሆኑ የአሰሪና ሠራተኛ ተወካዮች የሚጠይቁትን ድጋፍ ለማድረግ ቢሮው ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ በበኩላቸው የአሰሪውን ጥቅም በማይነካ መልኩ የሠራተኛውን መብት ለማስጠበቅ ኮንፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ኮንፌዴሬሽኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዘጠኝ ቅርንጫፍ ጽፈት ቤቶችን ከፍቶ በአሰሪና ሠራተኛ ህግና መመሪያ መሰረት የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ እየሰራ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ተወካይ አቶ አብዱርሀማን ቁብሳ በበኩላቸው "የአሰሪንና ሰራተኛውን የእርስ በርስ ግንኙነት አክብሮ መስራት የስልጣኔ ምንጪ ነው" ብለዋል።
ሠራተኛው መብቱን ለማስከበር ከሚያደርገው ትግል ጎን ለጎን በባለቤትነት ስሜት ስራውን ማከናወን እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል።
ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው የምክክር ጉባኤ ላይ የክልልና የፌዴራል ባለ ድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።