ቀጥታ፡

የአጭር፣ የመካከለኛ፣ የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል፣ የእርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ይጀመራል

ታህሳስ 6/2012 የኢትዮጵያ የአጭር፣ የመካከለኛ የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል፣ የእርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጀመራል። በሻምፒዮናው ከ30 ክለቦች የተውጣጡ 894 ሴትና ወንድ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና የውድድር የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ የሻምፒዮናው ዓላማ ለአትሌቶች የአጭርና መካከለኛ ርቀት እንዲሁም የሜዳ ተግባራት የውድድር ዕድል መፍጠር እንደሆነ ለኢዜአ ገልጸዋል። ክለቦች ልምድና ተሞክሮ የሚለዋወጡበት መድረክ መፍጠርና በየውድድር አይነቶቹ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራትም የሻምፒዮናው ዓላማዎች ናቸው ብለዋል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በመካከለኛ ርቀት እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ዕድል ያገኙ አትሌቶች በአህጉራዊ የውድድር መድረኮች መልካም የሚባል ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆነ ገልጸዋል። በአጭር ርቀትም ከማጣሪያዎች ባለፈ ወደ ፍጻሜ በማለፍ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን ተናግረዋል። ይህ ማለት ግን በአጭርና መካከለኛ ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ውድድሮች በቂ ስራ ተሰርቷል ማለት አይደለም ሲሉ ነው አቶ አስፋው የተናገሩት። የአሰልጣኞችን አቅም ከማጎልበትና የውድድር አማራጮችን ከማስፋት አኳያ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅም አመልክተዋል። በቅርቡ ከከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች ለተውጣጡ የአትሌቲክስ አሰልጣኞች ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነና ቀጣይነትም እንደሚኖረው ገልጸዋል። በተጨማሪም አሰልጣኞችን ለማብቃት በውድድር ዘርፎቹ የውጭ አሰልጣኞችን የመቅጠር ስራ በሂደት ላይ እንደሆነ ጠቅሰው ይህም 'አሰልጣኞቻችን ለማብቃት ያለው ሚና ወሳኝ ነው' ብለዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሻምፒዮናው ለሚሳተፉ አትሌቶች የ200 ሺህ ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የአጭር፣ የመካከለኛ የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል፣ የእርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ነገ ሲጀመር ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ። የፍጻሜ ውድድሮቹ የወንዶች ስሉስ ዝላይ፣ የሴቶች አሎሎ ውርወራና የ4X1500 ሜትር ድብልቅ /ወንድና ሴት/ የዱላ ቅብብል ናቸው። ከፍጻሜ ውድድሮቹ በተጨማሪም በወንዶችና በሴቶች በተመሳሳይ የ100 እና 800 ሜትር፤ የ400 ሜትር መሰናክል የማጣሪያ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። ነገ የሚጀመረው ሻምፒዮናው እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ይቆያል። መከላከያ የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ የአጭር፣ የመካከለኛ የ3000 ሜትር መሰናክል፣ የእርምጃና የሜዳ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም ፆታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም