ቀጥታ፡

የመንግስት ተሽከርካሪ በመስረቅ ሙከራ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ክስ ሊመሰረትበት ነው

ኢዜአ ታህሳስ 6/2012 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ንብረት የሆነ ተሽከርካሪ ለመስረቅ ሙከራ ካደረጉት ሶስት ግለሰቦች መካከል አንዱ ተጠርጣሪ ተይዞ በፖሊስ ክስ ሊመሰረትበት ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ አምባሳደር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ታህሳስ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ለሥራ የወጣ ንብረትነቱ የኢዜአ የሆነ ኮድ 4 የሰሌዳ ቁጥር 13276 ሶስት ግለሰቦች ተሽከርካሪ ከቆመበት በተመሳሳይ ቁልፍ ከፍተው ለማስነሳት ሙከራ ያደርጋሉ። ይህን ከርቀት የተመለከተው የመኪናው አሽከርካሪ ደርሶ መኪናውን ለመስረቅ  ሙከራ ሲያደርጉ ከነበሩት ሶስት ተጠርጣሪዎች ውስጥ አንዱን በመያዝ ለፖሊስ አስረክበዋል። እንደ አሽከርካሪው አቶ ደረጀ ዮሀንስ ገለጻ፤ መኪናውን ይዘው ለመሰወር ሙከራ ካደረጉት ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለቱ ሊያመልጡ ችለዋል። መኪናውን በተመሳሳይ ቁልፍ በመክፈት አስነስቶ ለመሰወር ሙከራ ያደረገው ተጠርጣሪ በቅርብ ርቀት ሆነው ላይ ሻይ ቡና ሲሉ የነበሩት አቶ ደረጀ በፍጥነት ወደ መኪናው አምርተው ተጠርጣሪውን በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አቶ ደረጀ በመኪናቸው የአሽከርካሪ መቀመጫ ላይ ተቀምጦ መኪናውን አስነስቶ ለመሰወር ሲሞክር እንደያዙትም ተናግረዋል። ስርቆት ለመፈፀም ሲል የያዙትን ተጠርጣሪ ግለሰብ በአካባቢው ለነበሩ የፖሊስ አባላት ሊያስረክቡ ጥረት ቢያደርጉም የዚህ ቀጠና አይመለከተንም ባሉ በአካባቢው የነበሩ የህግ አስከባሪዎች ምክንያት ተጠርጣሪውን ከሁለት ሰዓታት በላይ እጃቸው ላይ ለማቆየት መገደዳቸውን ይገልፃሉ። ወንጀሉ ከተፈፀመ በኋላ ከሁለት ሰዓታት በላይ ዘግይተው የደረሱት የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አባላት የያዙትን ተጠርጣሪ ቃላቸውን ሰጥተው እንዲረከቡ ያደርጋሉ። ይህን ካደረጉ በኋላ ጉዳዩን ለተቋማቸው የህግ ክፍል በማሳወቅ እንዲከታተለው አድርገዋል። ታዲይ ይህ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ዛሬ ለልደታ ክፍለ ከተማ 5ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ህግ ክፍል ባለሙያ ወይዘሮ ታደለች ቦጋለ አስታውቀዋል። የስርቆት ወንጀሉ በህዝብና መንግስት ንብረት ላይ የተቃጣ ጥፋት በመሆኑ ጉዳዩን በፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደሚከታተለው ተናግረዋል። ድሮ ድሮ የጎን መመልከቻ መስታወት (ስፖኪዮ)፣ ቴፕ እና ጌጣጌጦች ከመኪና ላይ ሲሰረቁ ይስማ የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ሙሉ መኪናው ወደ መስረቅ እንደተሸጋገረ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ በርካታ ህገ ወጥ ድርጊቶች ተበራክተዋል፡፡ በቀንና በምሽት የሚፈፀሙ ዝርፊያዎች ለነዋሪዎች ስጋት መሆናቸው በተደጋጋሚ እየተዘገበ ይገኛል። በሞተረኛና በመኪና የሚታገዝ ዝርፊያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አለም አቀፍ ዲፕሎማቶችም ጭምር ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሰዎች መኪናቸውን አቁመው መንቀሳቀስ እየቻሉ አለመሆኑን ይናገራሉ። ሰዎች መኪናቸውን ካቆሙበት ስፍራ እንደተወሰደባቸው ለፖሊስ ሪፖርት እንደሚያደርጉ በመገናኛ ብዙሃን ሲዘገብ ሰንብቷል። በመሆኑም የመኪና ስርቆት በአደባባይ የሚፈፀም አይን ያወጣ ስርቆት ስለሆነ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ የችግሩ ሰለባ ከመሆን ለጥቂት የተረፉት አቶ ደረጀ ጠይቀዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም