የኢትዮጵያ የባሕል ቡድን ወደ ኤርትራ አቀና - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕል ቡድን ወደ ኤርትራ አቀና
ኢዜአ፤ ታህሳስ 6/2012 በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት የተመራው የኢትዮጵያ የባሕል ቡድን ዛሬ ከሠዓት በኋላ ወደ ኤርትራ አምርቷል። የባሕል ቡድኑ በኤርትራ የአንድ ሣምንት ቆይታ በማድረግ የሙዚቃ ዝግጅት እንደሚያቀርብ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ቡድኑ ከውጭ ጉዳይና ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች፣ ከብሔራዊ ቲያትር፣ ከታዋቂ ድምጻዊያንና የጃኖ ባንድ የተውጣጡ ከ60 በላይ አባላትን መያዙ ተገልጿል። የባሕል ቡድኑ ጉዞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሠላም ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ተነግሯል። የባሕል ቡድኑ በኤርትራ ቆይታው በአስመራ፣ ከረን እና ምጽዋ ከተሞች የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። የኤርትራ የባሕል ቡድን ባለፈው የካቲት 2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ተመሳሳይ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ባህርዳር እና ሃዋሳ ከተሞች ማቅረቡ ይታወቃል።