የመቐለ-ደንጎላት፣ ሳምረ- ፊናርዋ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ መጓተት ጫና እያሳደረብን ነው ---ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመቐለ-ደንጎላት፣ ሳምረ- ፊናርዋ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ መጓተት ጫና እያሳደረብን ነው ---ነዋሪዎች
ኢዜአ ታህሳስ 6 ቀን 2012 የመቐለ- ደንጎላት ፤ ሳምረ-- ፊናርዋ የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጓተት በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑን ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ፣ የተጓተተውን የ93 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ውሉን ለወሰደው ለመከላከያ ኮንስትራክሽን ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቋል።
በመቐለ ከተማ የሰሜን ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ብርሃነ በሪሁ አካባቢያቸውን አቋርጦ የሚያልፈው የአስፋልት መንገድ ግንባታ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሯቸው እንደነበር ገልጸዋል።
“የግንባታው እንቅስቃሴ በተግባር ሲታይ የአፈር ቁፏሮ ሥራ ከማከናወን ባለፈ ሌላ ውጤት አላየንም፤ በእዚህም ዕለታዊ ስራች ላይ ጫና እየተፈጠረ ነው” ብለዋል አቶ ብርሃነ።
ለመንገዱ ግንባታ በተካሄደ ቁፋሮ ገደላማ ቦታዎች መብዛታቸውን የገለጹት ነዋሪው፣ ህጻናትና የዕድሜ ባለጸጎች በተቆፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ እየወደቁ ለአደጋ የተጋለጡበት ሁኔታ መከሰቱን አመልክተዋል።
“የመንገዱ ግንባታ የእለተ ተእለት ስራችንን እጅግ ፈተኝ አድርጎታል” ያለው ደግሞ በመቀሌ ከተማ በእንጨት እና በብረታ ብረት ማምረት ሥራ የተሰማራው ወጣት ሙሉዓለም ገብረሚካኤል ነው።
ለመንገዱ ግንባታ የመኖሪያ ቤታቸውና የድርጅታቸው መውጫና መግቢያ በር ተቆፍሮ በቀላሉ ለመንቀሳቀስመቸገራቸውን የገለጹት ደግሞ በሃውልት ክፍለ ከተማ የሚኖሩት መምህርት ርግበ አለማዮሁ ናቸው።
እንደ መምህርቷ ገለጻ የመንገዱን ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል ገብቶ ስራውን የጀመረው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ለችግሩ ተገቢ ትኩረት አለመስጠቱን ገልጸዋል።
የሚመለከታቸው የአመራር አካላት ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው መምህርቷ የጠየቁት።
“ለመንገዱ ግንባታ ሲባል የእርሻ መሬታችንን ለቀናል” ያሉት ደግሞ በሕንጣሎ ዋጅራት ወረዳ የደንጎላት ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ዲያቆን አርአያ ገብረመስቀል ናቸው።
“የግብርና ምርታችንን ለገበያ ለማቅረብና ከገበያ የምንፈልገውን ገዝተን ለማምጣት ይጠቅመናል ያልነው መንግድ ግንባታ መጓተት ህዝቡን ቅሬታ ውስጥ ከቶታል” ብለዋል።
በመንገዱ መጓተት ማዘናቸውን የገለጹት ዲያቆን አርአያ፣ ፈጥኖ አለመጠናቀቁ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ጠይቋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመቐለ-ደንጎላት፤ ሳምረ--ፊናርዋ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጂነር አክሊሉ አሰፋ በበኩላቸው፣ የመከላከያ ኮንስትራክሽን ግንባታውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም እንዲያስረክብ ውል ፈጽሞ እንደነበር አስታውሰዋል።
ኢንጂነር አክሊሉ እንዳሉት ግንባታው በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የመንገድ ፕሮጀክት ከአጠቃላይ ሥራው እስካሁን ድረስ የተጠናቀቀው 50 በመቶ ብቻ ነው።
ለመንገዱ ግንባታ መጓተት ዋና ምክንያት ውል የወሰደው ድርጅት ሥራውን ለማስጀመር የሚያስችለውን ማሽነሪ እና ሌሎች ግብአቶችን በበቂ ሁኔታ አለማቅረቡ እንደነበር ተናግረዋል።
“በየደረጃው የሚገኙ የመቀሌ ከተማ እና ሰሓርቲ ሳምረ ወረዳ አስተዳደር አካላት ከወሰን ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ጊዜ መውሰዳቸው ሌላው እንቅፋት ነው” ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ኮንስትራክሽን ግንባታውን በስድስት ወራት ጊዜ ወስጥ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ እንዲያስረክብ ግዴታ እንዲገባ ተደርጓል” ብለዋል ኢንጂነር አክሊሉ።
በመከላኪያ ኮንስትራክሽን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ግተት የመንገዱ ግንባታ ሥራ ከተባለው ጊዜ መዘግየቱን አመናዋል።
“አሁን በተጨመረው ጊዜ ውስጥ ስራውን ለማጠናቀቅ በየደረጀው ያሉ የአስተዳደር አካላት መንገዱ በሚያቋርጥባቸው አካባቢዎች የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን በማቃለል ሊያግዙን ይገባል” ብለዋል።
የተሰጣቸው ተጨማሪ ጊዜ ማነሱን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከ900 በላይ ሠራተኞችን፣ ጠጠር፣ ሬንጅና ብረቶችን ማቅረባቸውንና በተፈቀደላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚተጉ አስረድተዋል።
የግንባታ ሥራው እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ቢሯቸው እግዛ እንዲሚያደርግ ያረጋገጡት ደግሞ የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን፣ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረጻዲቅ ናቸው።