አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች ጋር በብልፅግና ፓርቲ ዙሪያ እየተወያዩ ነው

52
ኢዜአ ታህሳስ 5/2012 የአዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች ጋር በብልጽግና ፓርቲ ምስረታና መተዳደሪያ ደንቦች ዙሪያ እየተወያዩ ነው። የውይይቱ  ዓላማ የፓርቲው  ምንነትና የወደፊት ተግባራት ላይ ለአመራሩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን አዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን  እንደገለጹት በተለያየ መንገድ ይጓዙ የነበሩ አጋርና እህት  የፖለቲካ ድርጅቶችም ወደ አንድ መጥተው በሀገራቸው ጉዳይ እኩል መወሰንና መጠቀም እንዲችሉም ብልጽግና ፓርቲ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በተለይ ለሃገራዊ አንድነት፣ ሰላምና እኩል ተጠቃሚነት ውህደቱ አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ከዚህ  በፊት ይነሱ የነበሩ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን በመፍታት የጥንት ባህሎች፣ ወጎችና የጋራ ማንነቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል። "የደቡብ ወሎ ዞን አመራርም የፓርቲውን ዓላማ ለህብረተሰቡ በማሳወቅ ግቡን እንዲመታ በባለቤትነት ርብርብ ያደርጋል" ብለዋል፡፡ ውይይቱ ለሁለት ቀናት በሚያደረገው ቆይታ በብልጽግና ፓርቲ ምንነት፣ ህገ ደንብ፣ ፕሮግራሞችና ይዟቸዉ በመጣቸው ድሎች ዙሪያ ለተሳታፊዎቹ ማብራሪያ ይሰጣል። በውይይቱ ሂደት ከሚነሱ ሃሳቦች ግብዓት ይወሰዳል ተብሏል፡፡ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ባለው በውይይት  አንድ ሺህ የሚጠጉ የዞንና የወረዳ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን ለሚነሱ ጥያቄዎችም የአዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምላሽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም