በባቲ ከተማ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመስጠት የተጠረጠረ ግለሰብ ተያዘ

139
ኢዜአ ታህሳስ 5/2012 በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባቲ ከተማ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በመስጠት የተጠረጠረ ግለሰብን እጅ ከፍንጅ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ። የከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መሃመድ አሊ እንደገለጹት ሀሰተኛ ማስረጃ በመስራት በህገ ወጥ መንገድ የመጠቀም  ተግባር እየተስፋፋ መጥቷል። ሰሞኑን ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ  መሰረት  ፖሊስ ባካሄደው ፍተሻ  ከ170 በላይ የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ  ማግኘት መቻሉን አመልክተዋል። ከዚህም  ውስጥ    23 ተማሪዎች ከስምንተኛ ወደ ዘጠንኛ ክፍል አልፈዋል ተብሎ የተሰጣቸውና 115 የተለያዩ ኮሌጆች  ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ይገኙበታል። ከጉዳዩ ጋር ከተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች መካከል  አንደኛው ታህሳስ 2/2012 ዓ.ም በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ከሰነድ መስሪያ ቁሳቁሶችና ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙን ዋና ኢንስፔክተር መሃመድ አስታውቀዋል። የተያዘው ተጠርጣሪ  ጉዳዩ በህግ እየተጣራ እንደሚገኝና ቀሪው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገበት መሆኑን  አመልክቷል። "በከተማው በርካታ ህገ ወጥ ተግባራት በስውር እየተሰሩ ነው" ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ እነዚህን ህገ ውጥ ተግባራት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም