ከኦሮሚያ ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ለተፈናቀሉ ዜጎች ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

50
ሀዋሳ ሰኔ15/2010 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ የጌዴኦ ብሄር ተወላጆችን ለማቋቋም በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ። በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬና የፌዴራል አደጋ መከላከልና ብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሚመራ ቡድን ዛሬ በዲላና ገደብ የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ተዘዋውረው  ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ እንዳሉት በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ይኖሩ በነበሩ የጌዴኦና ጉጂ ኦሮሞ መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት የደረሰው ጉዳትና መፈናቀል ሊከሰት የማይገባውና ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ ግጭቱን ተከትሎ ከ642 ሺህ በላይ የጌዴኦ ብሄር ተወላጆች ተፈናቅለው በጌዴኦ ዞን ስድስት ወረዳዎችና ዲላ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 77 ማዕከላት በተጨናነቀ መልኩ መስፈራቸውን ተናግረዋል። ከቁጥሩ ብዛት የተነሳ አቅርቦቱ ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ችግር ለመፍታት ከሚመለከተው የፌዴራል አካል ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። በማረፊያ ቦታዎቹ በተለይ ነፍሰጡርና አራስ እናቶች እንዲሁም ህጻናት ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ቀጣይ ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል። የኢፌዴሪ ብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከፍላጎቱ ጋር ባለመመጣጠኑ እጥረቱ መፈጠሩን ገልጸዋል። በቀጣይም የተፈናቃዮቹን ቁጥርና የምግብ አቅርቦቱን በማመጣጠን ረገድ በተቻለ ፍጥነት የማስተካከል ስራ እንደሚከናወን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም