ቀጥታ፡

የልጅነት ልምሻ መከላከል ዘመቻ በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ

ኢዜአ ታህሳስ 5/ 2012 ዓ.ም በሶማሌ ክልል  የልጅነት ልምሻ /ፖሊዮ/ መከላከል ዘመቻ በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ ። ዘመቻው ዛሬ በተጀመረበት ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዩሱፍ መሀመድ እንደተናገሩት በጠብታ የሚሰጠው መከላከያው በክልሉ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ለማዳረስ ጥረት ይደረጋል።

በሽታው በልጆች ላይ ከመከሰቱ በፊት መደበኛ ክትባት ማጠናቀቅ  ይገባል። የአሁኑ ዘመቻ  ከአንድ ዓመት በፊት በክልሉ ዶሎ ዞን ቦኴ ወረዳ በአንድ የሦስት ዓመት ህፃን ላይ የተከሰተው ፖሊዮ መሰል በሽታ እንዳይዛመት አስቀድሞ ለመከላከል እንደሆነ ኃላፊው አመልክተዋል። በክልሉ ባለፉት ዓመታት በጤና ተቋማት ግንባታና በሰው ኃይል ስልጠና የተሻለ በመሰራቱ የክልሉ ጤና ሽፋን 64 በመቶ ደርሰዋል። በዚህ ልክ የክትባት ሽፋኑ ባለማደጉ ምክንያት  በተወለዱ በአንድ ዓመታቸው የክትባት ሽፋንን የሚያጠናቅቁ ሕፃናት 40 በመቶ ብቻ እንደሆኑ ጠቁመዋል። መደበኛ የክትባት ሽፋን ማነስ እንደምክንያት ያነሱት ማህበረሰቡ ለህፃናት ክትባት ያለው ግንዛቤ በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ እና አብዛኛው የህብረተሰቡ አኗኗር ዘይቤ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ነው። " ስለክትባቱ ጠቀሜታ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ይደረጋል" ብለዋል።

በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለውን የህፃናት ክትባት ለማሳደግ ወላጆች፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላትና የጤና ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳሰበዋል። ለአራት ቀናት ቤት ለቤት በጠብታ ለሚሰጠው መከላከያ  ዘመቻ  ማስፈጸሚያ ከፌዴራል መንግስት፣ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከህፃናት አድን ድርጅት አርባ ሚሊየን ብር መመደቡን የገለጹት በቢሮው የእናቶችና ህፃናት ጤና ማበልፀግ ቡድን መሪ አቶ አብዲሽኩር አብዲላሂ ናቸው። "በዘመቻው በአስራ አንድ ዞኖች፣ በስድስት ከተማ አስተዳደር፣ የተፈናቃዮች መጠሊያ ጣቢያዎች እና የስደተኞች ካምፕ የሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ አርባ ሺህ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉ "ብለዋል።በዘመቻው 219 ተሽከርካሪዎች ከ18ሺህ በላይ ባለሙያዎች ፣ተቆጣጣሪዎች እና በጎ ፍቃደኞች ተሰማርተዋል።

በጂግጂጋ ልጃቸውን ሲያስከትቡ የነበሩት ወይዘሮ ኢፍራህ ሰሌማን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ልጃቸውን ከበሽታው አስቀድመው መከላከል እንደሚችሉ ተገንዝበው ወደ ክትባት ጣቢያ  መምጣታቸውን ተናግረዋል።

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም