ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚኖሩት ስደተኞች እራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲደግፉ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ኢዜአ ታህሳስ 5/2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚኖሩት ስደተኞች እራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲደግፉ የሚያስችል ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ከተለያዩ አገራት በጦርነት፣ በድርቅና በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች  የሚመጡ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ የምትታወቅ ናት።

የሰብዓዊ ድጋፉ ላይ ከመረባረብ ባለፈም ስደተኞቹ በስራ እድል ፈጠራ እንዲታገዙና የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ የሚያስችል ፕሮግራም መዘርጋቱን ኤጀንሲው ገልጿል።

በኢትዮጵያ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ያላ  በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ስደተኞች በኢኮኖሚ  ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር እየተዘረጋ ነው።

ይህም ሁል ጊዜ ስደተኞችን በምግብና በጤና እያገዙ ከማስቀጠል ይልቅ በትምህርት ላይ የተደገፈ ሙያዊ ስለጠና በመስጠት እራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲረዱ የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።

በዚህም የስደተኞች ማቋቋሚያ ፕሮግራም ተቀርጾ፣ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበት እንዲጸድቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩንም ነው አቶ ያዕቆብ የገለጹት።

ይህም ስደተኞችን ብቻ ሳይሆን የስደተኛ ተቀባይ ማህበረሰብንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም እንደሆነ አንስተዋል።

ስደተኞች የሚኖሩበትን አካባቢ ያሉ እድሎች መሰረት ያደረገና የስደተኞችን ዝግጅትና ተነሳሽነት መሰረት ያደረገ እንደሆነ የተገለጸው ፕሮግራሙ፤ የስደተኞች አያያዝና ጥበቃ፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ላይ የሚያተኩር ይሆናል።

 የተዘጋጀውንም እስትራቴጂ ለልማት ድርጅቶችና ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማስተዋወቅ  ውይይት  እየተደረገበት መሆኑን አንስተዋል።

ከመጪው ሰኞ ጀምሮም በሲዊዘርላንድ ጄኔቭ ላይ የሚካሄድና ኢትዮጵያ በክብር እንግድነት የተጋበዘችበት መድረክ የሚዘጋጅ ሲሆን በዚህም መድረክ ላይ ይህ መረሃ ግብር አብሮ ለሚሰሩ የልማት ድርጅቶች የሚተዋወቅ ይሆናል ተብሏል።

በቅርቡ ስደተኞች የሚመሩበት አዋጅም ወጥቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁንም አቶ ያዕቆብ ገልጸዋል።

ለ10 ዓመታት የተቀረጸው ፕሮግራሙ በመጪዎቹ አመታት ስደተኞች  በእርዳታ እህል ላይ ጥገኛ ከመሆን ተላቀው ወደ አገራቸውም ሲመለሱ ባለሙያ ሆነው እንዲመለሱ ሊያደርጋቸው የሚያስችል ነው ተብሏል።

ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች የሚኖሩባት ኢትዮጵያ፣  ከ26 የዓለም አገሮች የመጡ ሲሆን፤ በ27 ካምፖች እርዳታና ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል።

የዓለም የስደተኞች ኮሚሽንና ተመድን ጨምሮ በርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የልማት ድርጅቶች ለስደተኞች እየሰጡት ያለው ትኩረት እየጨመረ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይም ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ይሄው ርብርብ መቀጠል እንደሚገባው ምክትል ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም