ወላይታ ድቻና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ጎል ተለያዩ

77
ሶዶ (ኢዜአ) ታህሳስ 4 ቀን 2012 ዓም ---በወላይታ በሶዶ ሁለገብ ስታድየም ዛሬ በተደረገ የኢትዮጵያ የወንዶች የፕሪሜር ሊግ ጨዋታ ወላይታ ድቻና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ጎል በአቻ ተለያዩ። በመጀመሪያው 45 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ግብ የማግባት ፉክክር ያልታየበትና ተጫዋቾቻቸው በመሀል ሜዳ ክፍል ላይ ኳስ በማንሸራሸር ተጠምደው የተስተዋሉበት ነበር ። በእዚሁ ክፍለ ጊዜ ኢላማውን የጠበቀ ቅብብሎሽ በማድረግና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ በኩል የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች በመጠኑ የተሻለ እንቅሰቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል ። በአንጻሩ ያለወሳኝ አጥቂው ወደሜዳ የገባው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን የወትሮውን ኳስ በመያዝ አስደንጋጭ የሆነ ሙከራ ሳያደርግና ተጋጣሚውን ማስጨነቅ ባለመቻሉ የቀድሞ አስፈሪነቱን አጥቶ የታየበት ነበር ። በፈጣን የኳስ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለተኛው 45 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ጫና በመፍጠርና የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ተሽሎ ታይቷል። ከክፍለ ጊዜው አጋማሽ ጀምሮ እስከ ፍጻሜው በነበረው የጨዋታ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች መካከል የነበረው ፉክክር ያልታየበት እንቅሰቃሴ ተመልካቹን ያሰለቸ ነበር ማለት ይቻላል። የወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ በሰጡት አስተያየት ተጋጣሚያቸው መከላከልን የመረጠ በመሆኑ አጥቅተው መጫወት እንዳልቻሉ ተናግረዋል ። "በውጤቱም ቅር ተሰኝቻለሁ" ብለዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ አቻቸው ሠርጅዮ በበኩላቸው ሜዳው ያሰቡትን የጨዋታ ፍሰት እንዳልፈቀደላቸው ገልጸው ከሜዳ ውጭ የተገኘ ውጤት በመሆኑ ያገኙት አንድ ነጥብ የማያስከፋ መሆኑን ገልጸዋል ። የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች እስከ ጨዋታው ፍጻሜ   ጨዋታውን በስፖርታዊ ጨዋነት ተከታትለውታል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም