በሃዋሳና በሲዳማ ዞን የተለያዩ ከተሞች በተከሰቱ ግጭቶች የተሳተፉ 226 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

70
ሀዋሳ ሰኔ 15/2010 በሃዋሳና በሲዳማ ዞን የተለያዩ ከተሞች በተከሰተ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ለማቋቋም ግብረ ሃይል አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን የሲዳማ ዞን አስታወቀ። ግብረ-ኃይሉ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ከ226 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎችን ለህግ መቅረባቸውም ተመልክቷል። ይሔንን አስመልክቶ የዞኑ ዋና አስዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት መነሻውን ሃዋሳ ያደረገው የሰሞኑ ግጭት በዞኑ አንዳንድ ከተሞችም ታይቷል። በግጭቱ ሳቢያ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ግጭቱን ለማረጋጋት ከተለያዩ አካላት ጋር እንቅስቃሴ መደረጉን ያስታወሱት አስተዳዳሪው የተፈናቀሉ ወገኖችን ማቋቋም የሚያስችል ተግባር በተቋቋመው ግብረ-ኃይል አማካኝነት መጀመሩን ተናግረዋል። ግብረ ሃይሉ የሃይማኖት አባቶችን የሃገር ሽማግሌዎችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችንና  ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ሲሆን በዞን፣ በወረዳና በከተማ ደረጃ የተዋቀረ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከሁለት ቀን በፊት ወደ ተግባር የገባው ግብረ ሃይሉ በየቀበሌው ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ተፈናቃዮችን የመለየት፣ የተዘረፉ ንብረቶችን የማሰባሰብ፣ የወደሙትንም የመለየት ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡ በችግሩ ውስጥ እጃቸው እንዳለባቸው የተጠረጠሩ ተሳታፊዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረቡ ሒደት በመጀመሩም እስካሁን 226 ግለሰቦች መያዛቸውን አስረድተዋል። “በክስተቱ ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ በወንዶ ገነት፣ በሃዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሻመና፣ በይርጋለምና ለኩ ከተሞች ጉዳት የደረሰ ሲሆን የንብረት ውድመቱ መጠን እየተጣራ ነው” ብለዋል። ከፍተኛ ውድመት በደረሰበት ለኩ ከተማ ከተጎጂዎች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን በየከተሞቹ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ያከናወኑትን ሰብአዊ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው የመመለሱ ሂደት የተሳካ እንዲሆን ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በሃዋሳ የተቀሰቀሰው ግጭት ከፍቼ ጫምባላላ በዓል ጋር አይገናኝም ያሉት አቶ አክሊሉ “በግጭቱ እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትን የማጣራቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም