ቀጥታ፡

በቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ አዲስ አበባ ፖሊስ መከላከያን አሸነፈ

ኢዜአ ታህሳስ 4 ቀን 2012 የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሲጀመር አዲስ አበባ ፖሊስ መከላከያን 3 ለ 2 በሆነ ውጤት የመጀመሪያ ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቋል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮ አዲስ አበባ ፖሊስና መከላከያ ባደረጉት የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስ በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በእያንዳንዱ ዙር ጨዋታዎች ላይ አንደኛው ጠንካራ ሌላኛው ደካማ ብቃት በማሳየት የተጫወቱ ሲሆን በጨዋታው ክለቦቹ ወጥ አቋም ሳያሳዩ ተጠናቋል።

አሸናፊው አዲስ አበባ ፖሊስ በኳስ ሰርብ በተደጋጋሚ ስህተቶችን የሰራ ሲሆን ቦታን ጠብቆ ከመጫወት አንጻርም ድክመት ታይቶበታል።

በመከላከያ በኩል የትኩረት ማጣት፣ የእርስ በርስ አለመናበብ እና ወደ ተጋጣሚው ቡድን የሚልኳቸው ኳሶች ተጋጣሚያቸውን ተጠቃሚ ያደረጉ ነበሩ።

የሁለቱን ክለቦች ትክክለኛ ብቃት ማየት ባይቻልም አዲስ አበባ ፖሊስ ከተጋጣሚው መከላከያ በአጨራረስ ብቃት የተሻለ ሆኖ በመገኘቱን አሸናፊ ለመሆን ችሏል።

ክለቦቹ ያደረጉት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ተካሄዷል።

ከጨዋታው በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ የቮሊቦል ክለብ አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ብሩ ሚኦ እንዳሉት፤ የውድድር ዓመቱን በድል መጀመር ለቀጣይ ጨዋታዎች ትልቅ ተነሳሽነትን ይፈጥራል።

''የአጨራረስ ብቃታችን ከተጋጣሚያችን የተሻለ በመሆኑ ጨዋታውን ልናሸንፍ ችለናል'' ያሉት አሰልጣኙ፤ በቀጣይ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ትምህርት ያገኙበት እንደሆነም ገልጸዋል።

''ጨዋታውን ከ2 ለ 1 መመራት ተነስተን ለማሸነፍ በቅተናል'' ያሉት ኢንስፔክተር ብሩ፤ የውድድር ዓመቱን በድል መጀመር ለቀጣይ ጨዋታዎች ተነሳሽነትና ብርታትን የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የቮሊቦል ክለብ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሊጉን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳለው አመልክተዋል።

የመከላከያ አሰልጣኝ መቶ አለቃ ወልደሰንበት ጳውሎስ በበኩላቸው ቡድኑ ጨዋታውን አሸንፎ የሚወጣበትን ዕድሎች አለመጠቀሙን በመግለጽ፤ የታዩ የቴክኒክ ድክመቶችን በማረም ለቀጣይ ጨዋታዎች ዝግጁ ሆኖ እንደሚቀርብም ተናግረዋል።

የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች ክለቦቻቸው የውድድር ዓመቱን በስፖርታዊ ጨዋነት ለማጠናቀቅ ስነ ምግባር ላይ ጠንካራ ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቮሊቦል ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ መስፍን አበራ እንዳሉት፤ የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን ጨምሮ የውድድሩ ተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ከፍ ብሏል።

በህዳር ወር 2012 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ እንዲካሄድ አቅጣጫ መቀመጡን እና ከክለቦች ጋር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ከፕሪሚየር ሊጉ በተጨማሪ ክለቦች በአፍሪካ ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮች እንዲሳተፉና ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት የወንዶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን የተቋቋመ ሲሆን በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ፤ በቮሊቦል ስፖርት ያለውን ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ችግር ለመፍታት የደቡብ እና አማራ ክልሎችን የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክትን የማጠናከር ስራ ይሰራል።

ነገ የመጀመሪያ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ቀጥለው ይካሄዳሉ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ከመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር ይጫወታሉ።

በክልል ከተሞች የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከአዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሶዶ ላይ የሚያካሂድ ሲሆን ሙገር ሲሚንቶ ከጣና ባህርዳር በተመሳሳይ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ሙገር ላይ ይጫወታሉ።

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻ አራት፣ ሙገር ሲሚንቶ ሦስት ጊዜ አሸናፊ በመሆን የሊጉን ዋንጫ ማንሳታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም