የሚኒስትሮች ም/ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የሚኒስትሮች ም/ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
ኢዜአ፤ ታህሳስ 4/2012 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 77ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የፌዴራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ስርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የመንግስት ፕሮጀክቶች አሰራርና አመራር ረቂቅ አዋጅ ዋናው አላማ የመንግስት አካላት በመንግስት ፕሮጀክቶች ውስጥ ያላቸውን ሃላፊነት በግልጽ በማመላከት ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን በማስፈን የፕሮጀክት ውጤታማነት እንዲጎለብት እንደሆነም ተገልጿል።
ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅ እና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
በምክር ቤቱ በሶስተኛ ደረጃ የታየው ጉዳይ በውጭ አገራት ስለተሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሳኔዎች እውቅና የመስጠትና የመፈፀም ስምምነትን ለማፅደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፤ በጉዳዩ ላይ ምክር ቤቱ በስፋት ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በቀረቡለት የተለያዩ ስምምነቶች እና የማፅደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ማስተካከያዎችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።