ቀጥታ፡

በጎንደር ለሚካሄደው የአገር ሽማግሌዎች ሕብረት ምስረታ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ጎንደር (ኢዜአ) ታህሳስ 4 ቀን 2012 ዓ.ም---አገር አቀፍ የሰላም ጥረቶችን ለማገዝ በጋሞ ሽማግሌዎች መሪነት በጎንደር ከተማ ለሚመሰረተው የአገር ሽማግሌዎች ሕብረት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የምስረታው አዘጋጅ የሆነው " ህብረ መንጎል" መልቲ ሚዲያ በጋራ በመሆን ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ "የህብረ መንጎል" መልቲ ሚዲያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ደግነት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‘’አብሮነት ከጋሞ እስከ ጎንደር’’ የተሰኘው አገር አቀፍ የአብሮነት የጉዞ ፕሮግራም 150 የአገር ሽማግሌዎችን በማቀፍ ይካሄዳል፡፡ የሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የአገር ሽማግሌዎችን፣ የወጣት ተወካዮችንና የመንግስት ባለ ድርሻ አካላትን ያቀፈው የልኡካን ቡድን በጉዞው በ6 የኢትዮጵያ የክልል ከተሞች በመዘዋዋር ስለ ሰላም ይመከራል፡፡ "የልኡካን ቡድኑ በሚያርፍባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ይመካከራል፡ ያበረታታል" ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ጉዞው የወጣቶችንና የሽማግሌዎችን ትስስር የማጠናከር ዓላማ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ "ልኡኩ የጉዞ መዳረሻ ባደረጋት የጎንደር ከተማም በየአመቱ በታላቅ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርአት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በመታደም አገር አቀፍ የሽማግሌዎች ህብረት እንዲመሰረት ያደርጋል" ብለዋል፡፡ ህብረቱ የአገር ሽማግሌዎች ልምድ እና የአስታራቂነት ሚና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይም አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚመክር ነው የተናገሩት፡፡ የሁሉም አካባቢዎች ያልተበረዘና ያልተከለሰ የሽምግልና ባህልን ወጣቶች ተረክበው እንዲያስቀጥሉትም  ወጣቶች የሚሳተፉበት የውይይትና የምክክር መድረኮች በየደረጃው እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር በሪሁን ካሳው በበኩላቸው "የጋሞ የአገር ሽማግሌዎች ግጭቶችን የፈቱባቸው የእርቅ ስነ-ስርቶች ጎንደርን ጨምሮ በአገሪቱ ለሚገኙ አካባቢዎች መልካም ተሞክሮ ይሆናል" ብለዋል ፡፡ "አገር በቀል የግጭት መፍቻዎችና የእርቅ ስነ-ሰርአቶች ለሰላምና መረጋጋት መሰረት ናቸው" ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ የአገር ሽማግሌዎቹ ተልእኮ እንዲሳካ ከተማ አስተዳደሩ ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ ሰብአዊ ቅርሶች እንዲመዘገብ በተወሰነበት ወቅት መከበሩ ጎንደር ከተማን ልዩ እንደሚያደርጋት ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ‘’አብሮነት ከጋሞ እስከ ጎንደር’’ የጉዞ ፕሮግራም በዛሬው እለት መነሻውን ከአርባ ምንጭ ከተማ በማድረግ የጉዞ ስንስርአቱ ጥር 14 ቀን 2012 በጎንደር ከተማ እንደሚያበቃ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም